ዓለምን የቀየሩ ሴት የሳይንስ ሊህቃን
ዛሬ ዓለም ዓቀፍ የሴት ሳይንቲስቶች ቀን ነው፣ ሳይንስ በአብዛኛው በወንዶች ቁጥጥር ሥር የወደቀ ዘርፍ ይመስላል፡፡
ገናና ስም ያላቸው ሳይንቲስቶች ይጠቀሱ ቢባል አልበርት አንስታይን፣ አይዛክ ኒውተን እና መሰሎቻቸውን ሊጠቅስ ይችላል፡፡
በርግጥ እኝህ ወንድ ሳይንቲስቶች ለዓለማችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ናቸው፡፡
ይሁንና ዘርፉ ዓለምን የሚቀይር ግኝት ያመጡ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ያሉበትም ጭምር ነው፡፡
ሴት ሳይንቲስቶች ከሸፈናቸው የታሪክ ጥላ ሥር ከወጡ ወዲህ በርከት ያሉ የዓለምን ታሪክ መቀየር የቻሉ ሴቶች መታየት ጀምረዋል፡፡
ሳይንቲስቶቹ በሳይንስ ብቻ ሳይሆን በፆታ ረገድ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ኢ-ፍትሃዊ አካሄድ መታገል የቻሉ ሲሆን፣ ሥኬታቸውም ዓለም ለሴቶች የነበራትን ግንዛቤ በመሠረታዊነት መቀየር አስችሏል፡፡
ዛሬ የካቲት 04 ቀን 2017 ዓ.ም የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን አስመልክተን በሳይንሱ ዘርፍ አስደማሚ ስኬት ከተጎናፀፉት መካከል ጥቂቶቹን እናስታውሳለን፡፡
እንግሊዛዊቷ የሂሳብ ሊቅ አዳ ላቭሌስ የተወለደችው በፈረንጆቹ 1815 ሲሆን፣ የሂሳብ ሊቅና ፀሀፊም ነበረች፡፡
በዘመናዊው ዓለም የሚሰጥ ዓይነት የዲግሪ ምስክር ወረቀት የላትም፡፡
ነገር ግን ባልተለመደ መልኩ የሂሳብ እና ሳይንስ እውቅና የተቸራት እና በዘመኗ ለነበሩ ሴቶችም አርአያ መሆን የቻለች ነበረች፡፡
ዓለም ዘመናዊውን ኮመፒዩተር ከመተዋወቁ በፊት አዳ ላቭሌስ የመጀመሪያዋ የኮምፒተር ፕሮግራመርም ነበረች፡፡
በ1867 የተወለደችው ፈረንሳዊቷ ፊዚስት እና ኬሚስቷ ማሪ ኩሪ የራዲዮ አክቲቪቲ ንጥረ ነገር ላይ ያደረገችው የምርምር ሥራዋ የመጀመሪያ ተጠቃሽ ሥራዋ ነው፡፡
በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ጥቅም ላይ የዋለው የሞባይል ኤክስ ሬይ (ራጅ) ከበርካታ የሳይንስ ግኝቶቿ መካከል አንዱ ነው፡፡
ከባለቤቷ ጋር በመሆን ፖሎኒየም እና ራዲየም የተሰኙ የራዲዮ አክቲቭ ንጥረ ነገሮችን በማግኘትም ይታወቃሉ፡፡
ኩሪ በሳይንሱ ዘርፍ ባበረከተቻቸው ድንቅ ግኝቶች ምክንያትም በፊዚክስ ዘርፍ በፈረንጆቹ 1903 የመጀመሪያዋ ሴት የኖቤል ሽለማት አሸናፊ ሆናለች፡፡
በመቀጠልም በኬሚስትሪ ዘርፍ ሁለተኛው የኖቤል ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡
ኩሪ በተለይም በቀዶ ሕክምናው ረገድ ለኤክስ ሬይ እድገት እና ለአቶሚክ ፊዚክስ ፊልድ መሠረት መጣል የቻለች በዓለም አቀፉ የሳይንስ ሴቶች ቀን የምትታወስ ድንቅ ሴት ናት፡፡
ሌላኛዋ ሊቅ ደግሞ በ1897 የተወለደችው ህንዳዊቷ ጃናኪ አማል ስትሆን የዕፅዋት ሳይንስ ሊቅ ናት፡፡
በሀገሯ የመጀመሪያዋ ሴት ሳይንቲስት እንደመሆኗ መጠን በዕፅዋትና በህዋ(ሳይቶሎጂ) ምርመራ ረገድ ቀላል የማይባሉ ሥራዎችን አበርክታለች፡፡
በአሜሪካ ትምህርቷን የተከታተለችው ጃናካ አማል በክርስቲያን ሴቶች ኮሌጅ እና የሸንኮራ አገዳ ብዜት ድርጅት ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግላለች፡፡
ሕይወቷ እስካለፈበት 1984 ድረስ በህንድ ሀገር ሪኮግኒሽን ኦፍ ቦታኒካል ሰርቬይ በተሰኘ ድርጅት ውስጥ እውቀቷን ሳትሰስት ሰጥታለች፡፡
ሕይወቷን ለዕፅዋት ሳይንስ በመስጠት በቅንነት ያሳየችው የሥራ ጥንካሬ እና ያመጣችው ውጤት ለትውልድ ትልቅ ተስፋን አጭሮ ማለፉ ዛሬም ድረስ ይነሳል፡፡
ቻይናዊቷ ፊዚስቷ ቺን ሹንግ ው በ1912 የተወለደች ሲሆን፣ በቻይና ከሚገኝ ናሽናል ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ በፊዚክስ የመጀመሪያ ድግሪዋን ተቀብላለች፡፡
የኤንሪኮ ፌርሚን የአቶሚክ ቲዎሪ በመከለስ በማሻሻል የመጀመሪያዋ ሴት ስትሆን የአቶም ክፍፍል ላይ ያተኮረው “ዉ ኤክስፐርመንት” በተባለው ሥራዋም በእጅጉ ትታወቃለች፡፡
ይህ ሥራዋ ወንድ ባልደረቦችዋ የነበሩት ቺን ኒንግ ያንግ እና ዶ/ር ሱንግ ዳኦ በ1957 ዓ.ም በዘርፉ ላሸነፉት የኖቤል ሽልማት መሠረት ጥሏል፡፡
ኬሚስቷ ሮሳሊንድ ፍራንክሊን እንግሊዛዊቷ ኬሚስት ፍራንክሊን በ1920 ተወለደች፡፡
የዘረመል አወቃቀር ላይ ያደረገችው ሥራዋ እጅግ አድናቆትን ያተረፈችበት ነው፡፡
ነገር ግን ጀምስ ዋትሰን እና ፍራንሲስ ክሪክ የተባሉ የዘርፉ ሰዎች ምንም እውቅና ሳይሰጧት ሥራዋን በስማቸው አሳትመዋል፡፡
ስመ ጥሯ ተመራማሪ ሳይጠበቅ በ37 ዓመቷ በማሕጸን ጫፍ ካንሰር ህይቷን አታለች፡፡
ይህ ምናልባትም ከኤክስ ሬይ ጋራ የተገናኘው የምርምር ሥራዋ ተጋላጭ ሳያደርጋት እንዳልቀረ ይገለፃል፡፡
ምናልባትም በህይወት ብትኖር ኖሮ በ1962 ባልደረቦቿ የወሰዱት የኖቤል ሽልማት የእሷ ሊሆን ይችል እንደነበርም ይገመታል፡፡
ማሬ ቃጦ