AMN-ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም
ዓለምአቀፍ መሪዎችን፣ ባለሞያዎችን እና የጉዳዩ ተቆርቋሪዎችን በአንድ ላይ በማምጣት እንዲወያዩ በማድረግ የጋራ ጥረቶቻችን ረሃብን በማጥፋት ለሁሉም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ርብርብ ፍሬ እንዲያፈራ እንደሚያስችሉ ተስፋ አለኝ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው፤ ለዓለም አቀፉ “ከረሃብ ነፃ ዓለም” ጉባኤ ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፤ ዓለምአቀፍ መሪዎችን፣ ባለሞያዎችን እና የጉዳዩ ተቆርቋሪዎችን በአንድ ላይ በማምጣት እንዲወያዩ በማድረግ የጋራ ጥረቶቻችን ረሃብን በማጥፋት ለሁሉም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ርብርብ ፍሬ እንዲያፈራ እንደሚያስችሉ ተስፋ አለኝ ሲሉም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በግብርና ሽግግር እና ምርታማነት ላይ በማተኮር የሠራነው ሥራ የታረሰ መሬታችን እጥፍ በማድረስ ከፍ ያለ እሴት ባላቸው የኢንደስትሪ አዝርዕት ምርት ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች አስገኝቷል ብለዋል።
በሚቀጥሉት ቀናት የጉባኤው ውይይቶች የጋራ ግቦቻችንን ስኬት የሚያፋጥኑ ታላላቅ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ እተማመናለሁ ሲሉም አክለዋል።