AMN – ህዳር 2/2017 ዓ.ም
አዲስ የፋይናስ ግብ እንደሚያስቀምጥ የሚጠበቀው ጉባኤው፤ እየጨመረ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ለመከላከል ሀገራት የሚያደርጉት የፋይናንስ ድጋፍ ሊጨምር እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ በሚመራው የአየር ንብረት ለውጥ ሳይንስና ትግበራ ተቋም ሃላፊ ዚንታ ዙመር ዛሬ የሚጀመረው ጉባኤ አዲስ የአየር ንብረት ለውጥ የፋይናንስ ግብ እንደሚያስቀምጥ ተናግረዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2009 ላይ የበለጸጉ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ለሆኑ ሀገራት በየአመቱ 100 ቢሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይሁንና አሁን ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ እየጨመረ በመምጣቱ የሚደረገውን ድጋፍ መጨመር ግዴታ በመሆኑ የዘንድሮው ጉባኤ ፋይናንስ ላይ ያተኮረ ይሆናል ብለዋል ሃላፊዋ፡፡
በምዕራብና በመካከለኛ አፍሪካ በሚገኙ 16 ሀገራት የሚኖሩ ከ7 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከባድ በሆነ የጎርፍ አደጋ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ነው የገለጹት፡፡
ሱዳን፣ ናይጀሪያ፣ ኒጀር፣ ካሜሩን እና ቻድ ከፍተኛ ጎርፍ ካስተናገዱ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የተባበሩት መንግስታት የድንገተኛ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል 38 ሚሊየን ዶላር የመደበ ቢሆንም በቂ አይደለም ያሉት ዚንታ ዙመር፤ የአየር ንብረት ለውጥን በበቂ ሁኔታ ለመከላከል በአንድ ዓመት ውስጥ ከ4 ትሪሊየን ዶላር በላይ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
እስከ አሁን ድረስ ግን ማን መክፈል እንዳለበት፣ ለምንና ምን ያህል መክፈል እንዳለበት የተደረሰ ስምምነት አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡
የበለጸጉ ሀገራት ለካርበን ልቀት ከሚያበረክቱት ከፍተኛ ድርሻ አንጻር የፋይናንስ ድጋፍ ድርሻቸውም ከፍተኛ ሊሆን ይገባል ሲሉ ታዳጊ ሀገራት ይከራከራሉ ሲል የዘገበው አፍሪካ ኒውስ ነው፡፡