AMN- ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ለብልጽግናና ብዝኃነት አደረጃጀት አባላት አዲስ አበባ ገቡ።
የአደረጃጀቱ አባላት ዛሬ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የመከላከያና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ተወካዮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የአደረጃጀቱ ፕሬዝዳንት ጋሻው በርቦ እንደተናገሩት፤ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማጠናከር ይገባል።
የተለያዩ ኮሚኒቲ ማኅበራትን በአባልነት ያቀፈው አደረጃጀትም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በገንዘብ ከመደገፍ ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተነደፉ አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይም እየተሳተፈ ነው ብለዋል።
ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ በማድረግ ያለንን አጋርነት ለማሳየት ኢትዮጵያ መጥተናል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ሠራዊቱ እየከፈለ ላለው መስዋዕትነትም ምስጋና አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት፤ በቀጣይም በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን የበለጠ በማቀፍና በማሳተፍ ለኢትዮጵያ የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ የበለጠ እንዲጎላ ርብርብ ይደረጋል።
የአደረጃጀቱ አባል ሰኢድ ቦሪ በበኩላቸው፤ ለውጡን ማስቀጠልና መከላከያን ለመደገፍ በማለም ኢትዮጵያ መጥተናል ነው ያሉት።
ሌላዋ አባል ዲዲሟ አግዋ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ተሳትፎ ስናደርግ ቆይተናል ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜም ከመንግሥት ጋር በመሆን ድጋፉን በምን መልኩ ማሳለጥ ይቻላል በሚለው ለመወያየትና ድጋፍ ለማድረግ መጥተናል ሲሉ አብራርተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ተወካይ ኮሎኔል ሲራጅ ሲንቢሩ በበኩላቸው፤ የዳያስፖራ አባላቱ ሠራዊቱ እየከፈለ ላለው ዋጋ እውቅና ለመስጠትና ለማመስገን መነሳታቸው የሚመሰገን ነው ብለዋል።
ሌሎች የዳያስፖራ አባላትም ይህንን አርዓያ በመውሰድ ከሠራዊቱ ጎን እንዲቆሙም ነው ጥሪ ያቀረቡት።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወንድወሰን ግርማ እንደገለጹት፤ ዳያስፖራ አባላቱ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ለመከላከያ ሠራዊት ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር በተለያዩ በጎ ተግባራት እንደሚሳተፉ ነው የገለጹት።
ዳያስፖራው አገሩን የሚያግዝበት በርካታ መንገዶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ በቴክኖሎጂ፣ በእውቀት ሽግግርና አገራዊ አጀንዳዎች ላይ የሚኖረው ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባም አጽንዖት መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አደረጃጀቱ በአሜሪካ የሚገኙ የተለያዩ ኮሚኒቲ ማኅበራትን በአባልነት ያቀፈ ነው።