ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ታሳቢ ያደረገ ፍትሐዊ የፋይናንስ ሥርዓት ሊዘረጉ ይገባል – አቶ አህመድ ሽዴ

You are currently viewing ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ታሳቢ ያደረገ ፍትሐዊ የፋይናንስ ሥርዓት ሊዘረጉ ይገባል – አቶ አህመድ ሽዴ

AMN- ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ታሳቢ ያደረገ ፍትሐዊ የፋይናንስ ሥርዓት ሊዘረጉ እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ጥሪ አቀረቡ።

አራተኛው የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በዚሁ ጊዜ፤ በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳቢያ ዓለም ባልተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ይገኛል ብለዋል።

ጎን ለጎንም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በዓለም ኢ-ፍትኃዊ የፋይናንስ ሥርዓት ምክንያት ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ነው ያስረዱት።

በመሆኑም ፍትሐዊ የፋይናንስ ሥርዓት በመዘርጋት የበለጸገች ዓለምን ለሁሉም ማዳረስ ይገባል ነው ያሉት።

ለዚህ ደግሞ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ታሳቢ ያደረገ ወጥና ፍትሐዊ አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ በበኩላቸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጋረጠውን የፋይናንስ ችግር ለመፍታት እንደዚህ አይነት ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ወሳኝ ናቸው ብለዋል።

ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ግጭትና ኮቪድ 19 ችግሩን አባብሰውት ቆይተዋል ያሉት ሚኒስትሩ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ አክሽን አጀንዳን እና አጀንዳ 2030ን ለማሳካት ቀጣይነት ያለው የልማት ግቦችን በበቂ ፋይናንስ መደገፍ ይገባል ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አካታች ሪፎርም ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸው፣ ሕገ-ወጥ የፋይናንስ ዝውውርን በጋራ መግታት ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በቂ ፋይናንስ ማቅረብና ትብብርና ቁርጠኝነትን ማሳደግ የቀጣይ የቤት ሥራ ሊሆን እንደሚገባም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው ጉባኤ በቀጣይ የፈረንጆች ዓመት በስፔን ከሚካሄደው 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ አስቀድሞ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

#Addisababa

#Ethiopia

ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!

https://linktr.ee/AddisMediaNetwork

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review