AMN – ታኀሣሥ 22/2017 ዓ.ም
በፈረንጆቹ 2024 ዓመቱን ሙሉ በየቀኑ የአንድ ማራቶን ርቀት የሮጠችው ቤልጂየማዊት ስሟን በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ለማስፈር ጥያቄ አቅርባለች፡፡
ሂልደ ዶሶግኒ የተባለችው ቤልጂየማዊት በዓመቱ በየቀኑ ማራቶን በመሮጥ የመጀመሪያዋ ሴት ለመሆን የሚያስፈልገውን አድርግያለው ብላለች።
ዛሬ በሩጫዋ የመጨረሻ ቀን የፍጻሜውን መስመር ስታልፍ በሰጠችው አስተያየት፣“ ሩጫውን በማጠናቀቄ እድለኛ ነኝ” ስትል ተናግራለች፡፡
የ55 ዓመቷ ሂልደ ዶሶግኒ በአንድ ዓመት ውስጥ በትንሹ 15 ሺ 444 ኪሎ ሜትር (9 ሺ 596 ማይል) መሮጥ ችላለች፡፡
ከሩጫው ባለፈም ለጡት ካንሰር ምርምር የሚውል 60 ሺ ዩሮ ወይም 62 ሺ 438 የአሜሪካ ዶላር አሰባስባለች።
የጂ ፒ ኤስ ፣ ፎቶ እና የቪዲዮ ማስረጃዎችን ጨምሮ በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ለመስፈር የሚያስችላትን ማስረጃዎች ማሟላቷንም ገልጻለች፡፡
ጥያቄዋ ተቀባይነት ካገኘ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ እውቅና እንደሚሰጣት ተመላክቷል ።
በዚህም 366 ቀናት በተከታታይ በመሮጥ የወንዶችን ክብረ ወሰን የያዘውን ብራዚላዊ ሁጎ ፋሪያስን ትቀላቀላለች ተብሏል።
በሴት ምድብ አውስትራሊያዊቷ ኤርካና ማሬ ባርትሌት በተከታታይ 150 ቀናት በመሮጥ ያስመዘገብችውን ክብረወሰን እንደምትሰብርም ይጠበቃል ሲል አልጀዚራ አስነብቧል፡፡