በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ አህመድ ሃሰን (ዶ/ር)፣ ‘የኢትዮጵያ ህዝቦች የፀረ-ቅኝ ግዛት ትንቅንቅ በዓድዋ ጦር ሜዳ’ በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው፣ ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን ቅኝ አገዛዝና ወረራን ለመከላከል ያደረጉት ትግልና ጥረት በህብረትና በአንድነት መንፈስ የተደረገ በመሆኑ ታላቅና አንፀባራቂ ድልን በታሪክ መዝገብ ላይ አስመዝግበዋል፡፡ ዓድዋ የዘመተው የኢትዮጵያ ሰራዊት ፍጹም ህብረ-ብሔራዊ እንደነበር በማውሳት፣ እገሌና እገሌ ሳይባባሉ ፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተና የንጉሰ-ነገስቱን ዓዋጅ ተቀብለው በሀገራዊ፣ በወገናዊና በባህላዊ ጉዳዮች የጋራ ትስስር፣ የጋራ መግባባትና ኢትዮጵያዊነት ወኔ ተሞልተው ታሪክ ለመስራት የተሰበሰቡ ዜጎች እንጂ ግዴታ፣ ሃይልና በህግ አስገዳጅነት የዘመቱ እንዳልነበሩ ይኸው የታሪክ ምሁር በጥናታቸው አጽንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል፡፡ በዚህ ዓምድም በዋናነት ኢትዮጵያውያን በጋራ ባደረጉት ተጋድሎ የሀገራቸውን ነጻነት ማስከበራቸውን የሚያወሱ የጥበብ ስራዎች ላይ አጭር ዳሰሳ እንደሚከተለው ተደርጓል፡፡
ደራሲና የቴአትር ባለሙያው ገዛኸኝ ድሪባ ዓድዋና ጥበብን መነሻ በማድረግ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጠው አስተያየት፣ ድሉ ለከያኒያን ትልቅ የንሸጣ (inspiration) መነሻ ነው ብሏል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ባለቅኔዎች በግጥም ስራዎቻቸው፣ አዝማሪዎች በመሰንቆና በክራራቸው፣ ሙዚቀኞች በሙዚቃ ስራዎቻቸው፣ ሰዓሊያን በዕይታ ጥበብ የፈጠራ ሥራዎቻቸው፣ ጸሃፌ ተውኔቶች በተውኔት ስራዎቻቸው፣ የፊልም ባለሙያዎች ደግሞ በፊልም ስራዎቻቸው ለማውሳት ጥረት ማድረጋቸውን ተናግሯል፡፡
ነገር ግን ይላል ደራሲና የቴአትር ባለሙያው ገዛኸኝ፣ ዓድዋን የሚያህል ዘመን አይሽሬ የነጻነት ድል በኪነ ጥበብ ሥራዎች ከዚህም በላይ ሊታሰብና ሊታወስ ይገባል፡፡ በተለይ ከያኒያን በፈጠራ ሥራዎቻቸው ተጋድሎውንና የድሉን ተምሳሌታዊነት ባልታየ ጎኑ ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው በመግለጽ ከፊታቸው ብዙ የቤት ሥራ አለ ሲል ተናግሯል፡፡
ግጥም
በሥነ ግጥም ሥራዎች ውስጥ ዓድዋን መነሻ አድርገው ከተቀኙ ባለቅኔዎች መካከል ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን አንዱ ነው፡፡ ‘እሳት ወይ አበባ’ በተሰኘው የግጥም መጽሕፉ “ዋ! ዓድዋ!” ሲል፤ የገዘፈ ተምሳሌትነቱን በቃላት ሃውልት ቀርጾ ለትውልዱ አኑሯል፡፡
…ዋ !
ዓድዋ የዘር አፅመ ርስትዋ
የደም ትቢያ መቀነቱዋ
በሞት ከባርነት ስርየት
በደም ለነፃነት ስለት
አበው የተሰውብሽ እለት
ዓድዋ …
የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ
የኢትዮጵያዊነት ምስክርዋ
ዓድዋ ..
ሎሬት ፀጋዬ በዚህ ግጥሙ፣ የሀገርን ነጻነት ለማስከበር የአበው መስዋትነትን ይዘክራል፡፡ የቀደምት ኩሩ ኢትዮጵያውያን ወኔና ጀብዱን ያወሳል፡፡ የነጻነት ትርጉም በዓድዋ ድል መንጸባረቁንም ያዜማል፡፡
ሌላኛው ገጣሚ ኪዳኔ መካሻ በአንድ ግጥሙ፤
“የማያረጅ ፈትል የማይወይብ ጥለት፣
ሕዝብ የፈተለው ሸምኖት በህብረት፣
በደም ጥለት ኩሎ የቋጨው ባንድነት…” ሲል ድሉ በህብረት የተገኘ መሆኑን ገልጿል፡፡ በደም ጥለት ኩሎ የቋጨው ባንድነት በማለት፤ የአንድነትን ወሳኝነትና የዓድዋ ድልም የዚህ ውጤት መሆኑን ያትታል፡፡

ሥነ ጥበብ
እንደ ዓድዋ ያሉ ታላላቅ ታሪካዊ ኩነቶች ለሥነ ጥበብ ትልቅ የፈጠራ መነሻዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ተጋድሎና የአሸናፊነት ስነ ልቦና፤ ብዙ መሰዋዕትነትና ጀግንነት ከጀርባቸው አስከትለው ስለሚመጡ በከያኒያን ስራዎችም ይህ ስሜት ይጋባል፡፡ ከዚህ አንጻር ድሉን ተከትሎ በኢትዮጵያ ስነ ጥበብ ውስጥ ከፍተኛ መነቃቃትን ብቻ ሳይሆን ወሳኝ የመከየኛ ርዕሰ-ጉዳይ መሆን ችሏል፡፡
በድህረ-ዓድዋ ዘመናዊ የስነ ጥበብ እንቅስቃሴ ውስጥም የኢትዮጵያን የድልና የተጋድሎ ታሪክን መሳል የተለመደ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰዓሊዎች ዓድዋን በትውፊታዊ የአሳሳል ዘይቤም ሆነ በዘመናዊው የአሳሳል ጥበብ ከይነውታል። በሰብአዊ አሳሳል ላይ በማተኮርም የኢትዮጵያን አርበኝነትና አልሸነፍ ባይነት በስነ ጥበባዊ ስራዎቻቸው አጉልተው ለማሳየት ጥረት አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ስነ ጥበብ አጥኚዋ ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ‘Modernist Art In Ethiopia’ በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት፣ የዓድዋን ድል ተከትሎ በኢትዮጵያ የስነ ጥበብ አከያየንና ዓላማ ላይ መሰረታዊ ለውጦች ታይቷል፡፡ ከዓድዋ በፊት የስነ ጥበብ ስራዎች በዋነኛነት ሀይማኖታዊ ይዘትና ዓላማ የነበራቸው ሲሆን፣ ከድሉ በኋላ ግን የስነ ጥበብ አከያየን ሂደት ላይ መሰረታዊ ለውጥ መጥቷል፡፡ ይህ ለውጥ በዋናነት እንደ ዓድዋ ያሉ ህዝባዊ ድሎች ለከያኒው ትልቅ ርዕሰ-ጉዳይና የላቀ ሀገራዊ ምናብ ስለፈጠረለት መሆኑን ጽፈዋል፡፡
ኤልሳቤጥ (ዶ/ር) በመጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት፣ ከድሉ በኋላ በከያኒያን ምናብና እሳቤ ላይ ሀገራዊ ንቃተ-ህሊና እንዲጎለብት አድርጓል፡፡ ከያኒያኑ የዓድዋ ድልን የመሰሉ ህዝባዊ የነጻነት ተጋድሎዎች እንዲጎሉና የላቀ ፋይዳ እንዳላቸው በስራዎቻቸው ማሳየት ችለዋል፡፡ ለአብነትም የአርበኞች ተጋድሎን፣ የዓድዋ ጀግና የጦር መሪዎችና ተያያዥ ስዕሎችን በመሳል የድሉን ታላቅነት በስራዎቻቸው አሳይተዋል። ለዚህም ማሳያ ከድሉ ማግስት ከተሰሩ ታላላቅ የስነ ጥበብ ስራዎች መካከል አንዱ የሰዓሊ በላቸው ይመር “የዓድዋ ድል” ስዕል እንደአብነት በመጽሐፋቸው ጠቅሰዋል፡፡
አዝማሪ፣ መሰንቆና ክራር
ዓድዋና ኪነ ጥበብን ስናወሳ በፍጹም ሊዘነጉ ከማይገባቸው ጥበበኞች መካከል አዝማሪዎች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ታላቅ ድል መሰንቆና ክራራቸውን አንግበው፤ የዘማቹን ወኔ በድፍረት ሲሞሉና ሲያነሳሱ፣ የወደቀውን ሲያጽናኑ፣ ያሸነፈውን ሲያሞግሱና ያጠፋውን በመውቀስ አዝማሪዎች ታግለው አታግለዋል፡፡ በጀግኖቹ ልብ የዘሩት ወኔም ነፃነትን አፍርቷል፡፡
ተክለፃድቅ መኩሪያ “አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት” በተሰኘ መጽሐፋቸው፣ ለዓድዋ አርበኞች የተዘፈነውና የተገጠመው ግጥም ብዙ እንደሆነ፣ የአብዛኞቹ አዝማሪዎች ስምም በውል እንዳልታወቀ ጠቅሰዋል። በስም ከተመዘገቡ አዝማሪዎች መካከል የወሎው ዐይነ ስውር አዝማሪ ሀሰን አማኑ አንዱ ነው፡፡ የጣይቱ ብጡል የቅርብ ተከታይ እንደሆነች የሚነገርላት አዝማሪት ጣዲቄም፤ በስም ከሚታወቁት ጥቂት አዝማሪዎች መካከል እንዷ መሆኗን የታሪክ አጥኚው በመጽሐፋቸው አስፍረዋል፡፡
ሁሌም ስለ ዓድዋና አዝማሪዎች ሲነሳ ዐይነ ስውሩ አዝማሪ ሀሰን አማኑ ወደ አዕምሮኣችን ከተፍ ይላል፡፡ በልቡ ብርሃን ጨለማውን እየሰበረ በዓድዋ ተራሮች ታሪክ ሰርቷልና፡፡
“ጣሊያን ገጠመ ከዳኛው ሙግት፤
አግቦ አስመለሰው በሠራው ጥይት፡፡
አሁን ማን አለ በዚህ ዓለም፤
ጣሊያን አስደንጋጭ ቀን ሲጨልም፤
ግብሩ ሰፊ ነው ጠጁ ባህር፤

የዳኛው ጌታ ያበሻ አድባር፡፡” እያለ ለወዳጆቹ ወኔን ያስታጥቅ ነበር፡፡
ተሾመ ብርሃኑ “ለዓድዋ ድል የአዝማሪዎች ሚና” ሲል ባሰፈረው ጽሑፍ እንደገለፀው፣ ሙዚቃ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ሕይወት ውስጥ ያበረከተውና እያበረከተው ያለው ድርሻ በዋዛ የሚታይ አይደለም። በተለይ ደግሞ ጥንታዊው የአዝማሪዎች ሀገረሰባዊ ሙዚቃ የኅብረተሰባችንን ደስታና ሐዘን፣ ብሶትና ቁጣን ለመግለፅ ከመዋሉ ባለፈ በደቦ ሥራዎች፣ በእርሻና ግንባታዎች ላይ እንደ ማበረታቻ በመሆን ጥቅም ላይ ውሏል። ሕዝባዊ እና ሀይማኖታዊ በዓላትም ላይ በከፍተኛ ሁኔታ አድምቋል፡፡ ሀገርን ለመታደግ በሚደረጉ አውደ ውጊያዎችም ላይ እንዲሁ እንደ አንድ መፋለሚያ መሣሪያ አገልግሏል።
ከሁሉም በላይ ግን ሙዚቃ ኅብረተሰብን በመሥራትና በመቅረፅ ረገድ የነበረው ሚና አይተኬ ነው። የምናደንቃቸው የትናንቶቹም ሆኑ የዛሬዎቹ ጀግኖቻችን ኃያልነታቸውና ብቃታቸው ከዘራቸው የተቀዳ፣ ከስፖርትና ከዳበረ አካላዊ ሥሪታቸው የተገኘ ብቻ አይደለም፤ ከበረታ ሥነ ልቦናም ጭምር እንጂ። ይህም ከመነሻው በጀግንነት፣ በተዋጊነትና በአሸናፊነት ዙሪያ ያለው የሕዝባችን አመለካከት ካኖረው ድርሻ የተቀዳ ሲሆን፤ በማሰራጨቱም ረገድ የአዝማሪዎቻችን ትጋት የበኩሉን አድርጓል።
ከላይ ከተጠቀሱት የኪነ ጥበብ አሻራዎች በተጨማሪ የሙዚቀኛ እጅግአየሁ ሽባባው (ጂጂ) ‘ዓድዋ’ ዓድዋን የሚያወሱ፣ የነጻነት አርበኞችን የሚያሞግሱና ተምሳሌትነቱን አጉልተው የሚያሳዩ የሙዚቃ ስራዎች ናቸው። እንዲሁም የፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ ‘አድዋ’ የተሰኘው ዶክዩመንታሪ ፊልም በሲኒማው ዘርፍ የሚጠቀስ የፈጠራ ሥራ ነው፡፡
ሌላው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በኪነ-ህንጻ ውበቱና ፋይዳው ብቻ ሳይሆን የድሉን ቅርሰ-ውርሶችንና ድሉን የሚያወሱ የስነ ጥበብ ስራዎች ለህዝብ እይታ በማቅረብ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የድሉ ኪነ ጥበባዊ ትሩፋቶች ወደ ህዝብ ቀርበው እንዲታዩ እድል ከመፍጠር በተጨማሪ፣ ከአድዋ ጋር የተያያዙ የስነ ጥበብ ስራዎችም በማሰባሰብ ረገድ ጉልህ ሚና እየተወጣ ይገኛል፡፡ እንዲህ አይነት የጋራ ታሪካዊ ድሎቻችንን የሚዘክር መታሰቢያ በቁጥር እየጨመሩ ቢሄዱ ለኪነ ጥበብ ስራዎች መጎልበት ቁልፍ ሚና እንደሚኖራቸው አያጠራጥርም፡፡
በአብርሃም ገብሬ