AMN- ጥቅምት 24/2017 ዓ.ም
ዘመቻ “ሰብል መሰብሰብ” በማወጅ በንቅናቄ ሰብሎችን በወቅትና በጊዜ መሰብሰብ ይገባል ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) አሳሰቡ፡፡
ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየጣለ ይገኛል ሲሉ አመልክተዋል።
ይህ ጉዳትም ጥቅምም አለው ሲሉ ጠቅሰዋል።
የመኸር አዝመራ በደረሰባቸው እና ሰብል መሰብሰብ በተጀመረባቸው አካባቢዎች ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ያሉት ሚኒስትሩ በነዚህ አካባቢዎች ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ሰብሉ ጉዳት እና ብክነት ሳይደርስበት በወቅቱ መሰብሰብ ይገባል ብለዋል።
ዘመቻ “ሰብል መሰብሰብ” በማወጅ በንቅናቄ ሰብሎችን በወቅትና በጊዜ መሰብሰብ እንደሚገባ አመልክተው በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ ሙያተኞች፣ ሠራተኞች፣ የፀጥታ አካላት፣ ተማሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ወዘተ… የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አመልክተዋል።
ባለሙያዎች የሚሰጡትን የጥንቃቄ ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ያሉ ሚኒስትሩ ሰብል ገና ባልደረሰባቸው፣ የመጀመሪያው ዙር የበልግ አዝመራ በሚካሄድበት፣ የበጋ መስኖ በተጀመረበት አካባቢ ደግሞ እየጣለ የሚገኘውን ዝናብ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ዕቅድ ከግብ የሚደርሰው የሚያጋጥሙንን ሁሉንም ችግሮች በተባበረ መንገድ በመሻገር ፣ መልካም አጋጣሚዎችን ደግሞ አሟጠን መጠቀም ስንችል ነው ሲሉም ገልጸዋል።