ዘመናዊ ዋና ከተማ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል – አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ

AMN – ጥር 8/2017 ዓ.ም

ዘመናዊ የሆነ ከተማን ለመፍጠር በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ሥራ አንድ ዋና ከተማ የሚያስፈልገው ልማት በመሆኑ ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ተናግረዋል።

ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረጉት ባለሙያው፣ በአዲስ አበባ እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶች የሚፈለገውን ዓይነት ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አዲስ አበባ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ መቀመጫ እንደመሆኗ ስሟን የሚመስል ከተማ ለመፍጠር የተሠራው ሥራ ዘመናዊ እና ጥራት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በኮሪደር ልማቱ የፈረሱ ቤቶች ለመኖር ምቹ እንዳልነበሩ መታዘባቸውን አውስተው፣ አሁን ላይ ነዋሪዎች የተሻለ መኖሪያ እንዲያገኙ መደረጉ የሚመሰገን ተግባር ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ከአዲስ አበባ እንዲወጣ ግፊት ሲደረግ እንደነበርም አስታውሰው፣ በከተማዋ የተሠራው ልማት ለዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ የሚመጡ እንግዶች ተጨማሪ ቀናትን እንዲቆዩ የማድረግ አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።

ይህም ሀገሪቱ የቱሪዝም ገቢዋ እንዲጨምር ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት አቶ ዘመዴነህ።

የአዲስ አበባ መለወጥ ለሀገር የሚጠቅም ነው ያሉት ባለሙያው፣ መሰል ሥራዎችን ለማጠናከር የሚችሉ ተቋማትን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

በሰፊና ሁሴን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review