ዘመን ተሻጋሪው ወዳጅነት

ኢትዮጵያ በዓለም የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት ከሆኑ ጥቂት የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ሀገርም ነች፡፡ ለዚህ በሚሊዮን የሚቆጠር እድሜ ያላቸው የ“ሉሲ”፣ “ሰላም” እና “አርዲ” የሰው ልጅ ቅሪተ አካሎች ጥናት (የአርኪዎሎጂ) ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

ኢትዮጵያ  ከጥንት  ጊዜ  ጀምሮ  ከተለያዩ  ሀገራት  ጋር  ግንኙነቶችን  ስታደርግ  ኖራለች። ከነዚህ  መካከል ጎረቤት  ከሆኑት የአረብ  ሀገራት ጋር ያለው  ግንኙነት  ይጠቀሳል፡፡

ኢትዮጵያ ከአረቡ ዓለም ህዝቦች ጋር ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት አላት፡፡ የታሪክ ተመራማሪው አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያና አረብ ግንኙነት የሰው ልጅ በምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነበረ ነው፡፡ ሁለቱ ህዝቦች በደም የተሳሰሩ፣ በባህል፣ ቋንቋ፣ ንግድ፣ ፀጥታና የተለያዩ ዘርፎች ግንኙነትና ትብብሮችን አድርገዋል፡፡

የታሪክ ተመራማሪው አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር)

በቅርብ ዓመታት እየወጡ ያሉ የዘረመል (ዲ ኤን ኤ) ጥናቶች በኢትዮጵያና የአረብ ህዝቦች መካከል ከፍ ያለ የደም ትስስርና ዝምድና እንዳለ ያሳያሉ፡፡ በቋንቋ ረገድም የአረቡ ዓለም ዋነኛ መግባቢያ ቋንቋ የሆነው አረብኛ የሴሜቲክ ቋንቋ ቤተሰብ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ከሴማዊ የቋንቋ ግንድ የሚመዘዙ በስፋት የሚነገሩ ቋንቋዎች ይገኛሉ። የሳባውያን ፊደል እና ኢትዮፒክ ፊደል ብዙ የሚመሳሰልና የተወራረሰ ባህርይ አላቸው፡፡ በቤት አሰራር፣ በእርሻ አስተራረስ ጥበብ በሁለቱ መካከል እርስ በርስ መወራረስ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

አህመድ (ፕ/ር) እንደሚሉት፤ በሁለቱ አጎራባች ህዝቦች መካከል ቀይ ባህር የሚገኝ ሲሆን፤ ቀይ ባህር ሁለቱን የሚለያይ ይሁን እንጂ እንደ ድልድይ ሆኖ ነው ሲያገለግል የኖረው፡፡ በእምነት ረገድም ሦስቱ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች ማለትም ይሁዲ፣ ክርስትና እና እስልምና መምጣት በፊትም ሆነ ከመጡ በኋላ አንዱ የሌላውን በመከተልና በመወራረስ ኖረዋል፤ እየኖሩም ይገኛሉ፡፡

በእስልምና አስተምህሮ የአብርሃም ሃይማኖት የሚባሉት ይሁዲ፣ እስልምና እና ክርስትና የመሰረቱት የይስሃቅና እስማኤል ዘሮች ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ ሦስቱም በአንድ አምላክ የሚያምኑ መሆናቸው ያስተሳስራቸዋል፤ ግንኙነታቸውም ከጥንትም ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ ይሁዲ፣ ክርስትና እና እስልምና ከመካከለኛው ምስራቅ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በአንድ አምላክ ማምለክን የሚያጠናክር ሆኗል፡፡

የታሪክ ተመራማሪው ላጲሶ ጌታሁን   (ፕ/ር) “የኢትዮጵያዊነት ታሪካዊ መሰረቶችና መሳሪያዎች” በሚል ርዕስ በፃፉት መጽሐፍ ላይ እንደሰፈረው፣ “‘በአረቦች አል አሀበሽ፣ አል ሀበሻ፣ ሀበሻት፣ ሀብሻት’ ተብለው በልዩ ልዩ የነጠላና የብዙ ስሞች የሚታወቁ ኢትዮጵያውያን ሰፋሪዎች (በአረቢያ ምድር ይኖሩ የነበሩ) ለረጅም ዘመን በሁለቱ የኢትዮጵያና አረብ ህዝቦች መካከል በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በባህልና በዘር ዘላቂ የመገናኛ መንገድና ድልድይ መስራች ህዝቦች ናቸው፡፡”

በርካታ ኢትዮጵያውያን በእስልምና ሃይማኖት ምስረታና ግንባታ ዘመን ከነብዩ ሙሐመድና ወራሽ ከሊፋዎች ጋር ተሰልፈው ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ነብዩ ከመወለዳቸው በፊትም ሆነ  በኋላ በአስተዳደጋቸው የሀበሾች ሚና ከፍተኛ እንደነበር የታሪክ ተመራማሪው አህመድ ዘካሪያ ያስረዳሉ፡፡

በነብዩ ሙሐመድ እድገት ትልቅ ሚና ከነበራቸው መካከል ኡሙ አይመን አንዷ ናቸው፡፡ ነብዩ አባታቸው አብዱሏህን ብቻ ሳይሆን እናታቸው አሚና በልጅነታቸው ሲሞቱ አደራ የተቀበሉ፤ ተቀብለው ነብዩ ሙሐመድን በእጆቻቸው ታቅፈው ሙቀት የለገሱና አንገታቸው ላይ አስደግፈው ያስተኙ ኡሙ አይመን ናቸው፡፡ ነብዩ ሙሐመድን እንደ እናት ሆነው ጡት እያጠቡ ያሳደጉ፣ “ከእናቴ ቀጥሎ ሁለተኛ እናቴ” ብለው የመሰከሩላት ሴት ኢትዮጵያዊት እንደነበሩም አህመድ (ፕ/ር) ያነሳሉ፡፡

የነብዩ ሙሐመድ የቅርብ ጓደኛና ረዳት የነበረው፣ “ቀዳማዊ ሙአዚን” የሚሰኘው ድምፀ-መረዋው ቢላል ሌላው በእስልምና ሃይማኖት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ቢላል ከነብዩ ሙሐመድ ታላላቅ የሃይማኖትና የጦር ባለስልጣኖች አንዱ ነበር፡፡ በአንድ አምላክ ማመንን በተግባር ያስመሰከረ ጀግና ነው፡፡ የመጀመሪያውን የሶላት ወቅት ጥሪ (አዛን) የማሰማት እድልም የተሰጠው ለቢላል ነው፡፡ እስልምና የቀለም ልዩነት እንደማይገድበው የቢላል መገኘት ማሳያ እንደሆነ አህመድ (ፕ/ር) ያነሳሉ፡፡

ነጃሺ አስሓማ ሌላኛው በእስልምና ሃይማኖት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው፣ በኢትዮጵያና አረቡ ዓለም መካከል ባለው ግንኙነት ከፍተኛ ሚና ያላቸው ኢትዮጵያዊ ንጉስ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ615 የመጀመሪያዎቹ የእስልምና እምነት ተከታዮች በመካ የቁረይሽ ባለስልጣኖች እጅ መከራና ስቃይ ሲደርስባቸው፣ በነፃነት ሃይማኖታቸውን እንዳይተገብሩ ሲሳደዱ፣ ነብዩ ሙሐመድ “ወደ ሐበሻ ተሰደዱ፤ በእርሷ አንድ ንጉሥ አለ። ከእርሱ ፊት ማንም ተበዳይ አይሆንም።  (ስለዚህ ተሰደዱ)፤ አላህ ካላችሁበት ሁኔታ አውጥቶ ድል እስክንጎናጸፍ ድረስ” (ሙሐመድ ጦይብ ኢብን ሙሐመድ ኢብን ዩሱፍ፤ “ኢትዮጵያ እና ኢስላም” በሚል መፅሀፋቸው ላይ እንደሰፈረው፡፡

በዚያን ጊዜ ማዕከሉን አክሱም አድርገው ያስተዳድሩ የነበሩት ነጃሺ ወደ ሃገሩ ለገቡ የመጀመሪያ ሙስሊም ስደተኞች የጥገኝነትና የሃይማኖት ነፃነት መብት እንዲሁም ለእስልምና ሃይማኖት በዓለም ላይ የመጀመሪያውን የእምነትና የፖለቲካ እውቅና የሰጡ አስተዋይ የሀገር መሪ ናቸው፡፡

አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር) እንደ ሚያስረዱት፣ በቁሬይሾች የሚደርስባቸውን መሳደድና ጭቆና ለማምለጥ የመጀመሪያ የእስልምና ሃይማኖት  ተከታዮች ሁለት ጊዜ ያህል ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል። መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በቁጥር አነስተኛ የነበሩ ወደ 15 አካባቢ የሚሆኑ ናቸው፡፡ ችግሩ ተፈቷል ተብለው ተመልሰው ቢሄዱም ገና እንዳልተፈታ ሲረዱ 83 አካባቢ ሆነው እንደገና ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡

የነብዩ ሙሐመድ ልጅ ሩቅያና ባሏ ኡስማን፣ የሦስተኛው ከሊፋ ኡስማን የአጎት ልጅ ሀምዛ እና ሌሎችም ለ15 ዓመታት ገደማ በኢትዮጵያ ደህንነታቸው ተጠብቆ በሰላም ኖረዋል፤ አንዳንዶቹም እዚህ ኖረው ህይወታቸው አልፏል፤ መቃብራቸውም ይገኛል፡፡ 

የመጀመሪያ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ከተቀበሉት ንጉስ ነጃሺ ዘንድ የመካ ቁሬይሾች መልዕክተኛ በመላክ አባብለው ለመውሰድ ቢሞክሩም “ምንም ብታደርጉልኝ፤ የእጅ መንሻ ብትሰጡኝ ከዚህ አይወጡም” በማለት ታድገዋቸዋል። ንጉሱ ስደተኞችን በአክብሮትና በስርዓት በማስተናገድ የኢትዮጵያውያን የእንግዳ ተቀባይነት ተምሳሌት ናቸው፡፡ ምንም ዓይነት መደለያ ባለመቀበልና ለስደተኞች ጥበቃ በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አክብሮት ያገኙ መሪ መሆናቸውንም አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር) ያስረዳሉ፡፡

አሁን ላይ በትግራይ ክልል ውቅሮ አካባቢ የሚገኘውን የነጃሺ መስጂድና መቃብር ለማልማት እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በእስልምና እምነት ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው ታሪካዊ ስፍራዎች አንዱ ነው፡፡ በእስልምና ሃይማኖት በቅድስና ቀዳሚዎቹ መካ እና መዲና ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ እስልምና መዲና ከመደረሱ ሰባት ዓመት አስቀድማ ነበር የተቀበለችው። የነጃሺ መስጂድ በአፍሪካ ካሉ ጥንታዊ፣ ታሪካዊና ቀዳሚዎቹ መስጂዶች ዋናውና አንዱ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ጥናትና ምርምር በማድረግ የበለጠ እንዲታወቅ መስራት እንደሚገባም አህመድ (ፕ/ር) ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአረቡ ዓለም ህዝቦች ጋር ያላት ግንኙነት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የነበረና በደም የተሳሰረ ቢሆንም ግንኙነቱን የሚያበላሹ ክስተቶች አልነበሩም ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ ከመስቀል ጦርነት ጀምሮ “ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት” የሚለውን ሀሳብ ለማስረፅ በብዙ መልኩ ተሞክሯል፡፡ ምዕራባውያን “ከእኛ በፊት ክርስቲያን የነበረች ሀገር ናት” በሚል ከአረብ ጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማዳከምና ለማራራቅ ሰርተዋል፡፡

አህመድ (ፕ/ር) እንደሚገለፁት፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያ የእስልምና እምነት ተከታዮችን በአክብሮትና በፍቅር በማስተናገድ ላደረጉት ውለታ በማሰብ ነብዩ ሙሐመድ “ኢትዮጵያን አትንኩ” የሚል ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ይህ ትዕዛዝም በመካከለኛው ምስራቅ በተነሱ የእስልምና መሪዎች ዘንድ የማይሻርና ጥብቅ መመሪያ ተደርጎ ሲወሰድ የኖረ ነው፡፡ በሙስሊሙ ዓለም ኢትዮጵያን መንካት ማለት ኃጢያት እንደ መስራት ይቆጠራል፡፡ 

እንደ ኡሙ አይመን፣ ቢላል፣ ነጃሺ ያሉ ስብእናዎች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሙስሊሙ ዓለም በጠቅላላው ትልቅ ቦታ ያላቸው ናቸው፡፡ ሙስሊሞች በብዛት ባሉባቸው    እንደ   ኢንዶኔዥያ፣  ማሌዥያ፣ ፓኪስታን ባሉ ሀገራት ወይም ሌላ ሀገር ሄደን “ከቢላል ሀገር የመጣሁ ነኝ” ብንል በክብር ነው የሚቀበሉን፡፡ ኢትዮጵያውያን ከነብዩ ሙሐመድ ቤተሰቦች ጋር የነበራቸው ትስስር በተለይ የነብዩ  ልደታቸው (መውሊድ) ሲታወስ ወይም ታሪካቸው ሲነሳ አብሮ የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ትልቅ እድል የእስልምና እምነት ተከታይ ሀገራት ዜጎችን በመሳብ እንደ ቱሪዝም መስህብነት በሚፈለገው ልክ እስከአሁን መጠቀም አልቻልንም፡፡ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ብቻ ሳትሆን የእስልምና እምነት መሰረቶች ከሚባሉት ግለሰቦች ጋርም ትስስር ያላት በመሆኑ በአግባቡ ብትጠቀምበት ከቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ገቢ ማግኘት እንደምትችል የታሪክ ተመራማሪው አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር) ያስረዳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ዓለም ከአንድ መንደር ወደ አንድ ቤት፤ ከአንድ ቤት ወደ አንድ ሞባይል እየተቀየረ መጥቷል፡፡ ዛሬ ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የአረብ ሀገራት በመሄድ በተለያዩ ስራዎች ተቀጥረው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ የአካባቢውን ባህል፣ ወግና ቋንቋ እየተረዱ ትስስሩም እየተጠናከረ መጥቷል፡፡

ፕ/ር አህመድ እንደሚገልፁት፣ ኢትዮጵያና የአረቡ ዓለም ሀገራት በጋራ አብረው ለማደግና ለመበልፀግ ሊተባበሩ የሚችሉባቸው ብዙ ዕድሎች አላቸው፡፡ እንደ ሳዑዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ፣ ኩዌት፣ ኦማን፣ ባህሬን፣ የመንና የሌሎች የአረብ ሀገራት የአየር ፀባይ ደረቅና ለግብርና ምርት የማይመች በመሆኑ የሚያስፈልጋቸውን የግብርና ምርቶች የሚያስገቡት በብዛት ከውጭ ሀገር ነው፡፡

በአንፃሩ ኢትዮጵያ ሰፊና የሚታረስ ለም መሬት፣ ውሃ፣ ማዕድንና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች ሀገር ናት፡፡ በቅርብ ርቀት የምትገኝ፣ በአፍሪካ ሁለተኛ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ያለች ተስማሚ የቱሪዝም መዳረሻ መሆን የምትችል ሀገር ናት፡፡ ብዙዎቹ የአረብ ሀገራት ፈጣሪ የሰጣቸውን እንደ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ያለውን የተፈጥሮ ፀጋ በመጠቀም ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም ፈጥረዋል፡፡

ከዚህ አንጻር የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ ልማት ያላቸውን መዋዕለ ንዋይ ሊያፈሱባቸው የሚችሉበት የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል ለማግኘት ወደ አረብ ሀገራት የሚያደርጉትን ጉዞ በስርዓት እንዲመራ ማድረግ ይገባል፡፡ በህጋዊ መንገድ ሄደው መብታቸው ተጠብቆ፣ ገቢ የሚያገኙበትን መንገድ በመፍጠር ቤተሰብም ሆነ ሀገር ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የኢኮኖሚ እና የባህል ዲፕሎማሲን በማስፋፋት ረገድ የተጀመሩ ጥረቶችን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ እና አረቡ ዓለም የጋራ የሆነ ጥቅም አላቸው፡፡ የእኛ ፖሊሲ ጎረቤት አቀፍና ሰላማዊ እስከሆነ ድረስ ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የታሪክ ተመራማሪው አህመድ (ፕ/ር) ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአረቡ ዓለም ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነትና ትስስር ጥልቅና ዘመንን የተሻገረ ነው፡፡ ዘርፈ ብዙ መልክና ገፅታም አለው። በቅርብ ጊዜ በተለይ ከስድስት ዓመታት ወዲህ በሁለቱ መካከል ያለው ወዳጅነትም እየተጠናከረ መጥቷል፤ ወደፊትም ከዚህ በላይ እያደገ ሊሄድ የሚችልበት ሰፊ እድሎች አሉት፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review