የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ከአስከፊ ህይወት ወጥታችሁ ስልጠናችሁን በብቃት በማጠናቀቅ ለምርቃት የበቃችሁ እንዲሁም ወደ ስራ ለመሰማራት የተዘጋጃችሁ ልጆቻችን እና እህቶቻችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ለማህበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊ እና ለስነ ልቦና ስብራት የተጋለጡ ሴቶችን ካሉበት የህይወት ውጣ ውረድ እንዲወጡ በማድረግ፣ የስነ ልቦና ድጋፍ እና የሙያ ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ በማሰማራት ላይ የሚገኝ ማዕከል ሲሆን፣ በ2ኛው ዙርም በ17 የሞያ አይነቶች የብቃት ምዘና ያለፉ 380 ሰልጣኞችን አስመርቀን የስራ እድልም ተፈጥሮላቸዋል በማለት ገልጸዋል።
ለማዕከሉ ድጋፍ በማድረግ እና የስራ እድል በመፍጠር ላይ የምትገኙ ባለሀብቶች እንዲሁም ሰልጣኞቹ በማዕከሉ በነበራቸው ቆይታ እናትም አባትም ሆናችሁ ከስልጠና በላይ የሆነ እንክብካቤ እና ፍቅር በመስጠት ከልብ ያሰለጠናችሁ፣ የተንከባከባችሁ እና ወደ ስራ ያሰማራችሁ አመራሮች እና መምህራንን በሰልጣኞቹ እና በራሴ ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ ሲሉም አክለዋል።