ዛሬ የጣይቱ የባህል እና የትምህርት ማዕከልን መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing ዛሬ የጣይቱ የባህል እና የትምህርት ማዕከልን መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ሚያዝያ 18/2017

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ የጣይቱ የባህል እና የትምህርት ማዕከልን መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ብለዋል፡፡

120 ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ የቅርስ ቤት የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የንግድና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የአዲስ አበባ 2ኛ ከንቲባ የነበሩት ቢትወደድ ኃይለጊዮርጊስ ኃይለሚካኤል መኖሪያ ቤት እንዲሁም የመጀመሪያ የማዘጋጃ ቤት እና የፍትህ ማዕከል ሆኖ ያገለገለ ታሪካዊ ቤት ነው።

በተወዳጇ አርቲስት ዓለምፀሃይ ወዳጆ አስተባባሪነት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 39 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም በርካታ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዉበት ውብ ሆኖ ታድሷል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከተማችንን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ ከሰራናቸው ስራዎች ጎን ለጎን፣ ከተማችንን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ቅርሶችን አድሰን የከተማችን ተጨማሪ ውበት እና የቱሪስት መስህብ ለማድረግ በርካታ ስራዎችን የሰራን ሲሆን፣ ለአብነትም በፒያሳ አካባቢ ያሉ የቅርስ ስፍራዎች ይዘታቸውን ሳይለቁ አቧራቸው ተራግፎ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ታድሰው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ አድርገናል።

ይህ የባህልና የትምህርት ማዕከል ለከተማችን ከሚሰጠው የቱሪስት መዳረሻነት በተጨማሪ ለሃገራችን ተተኪ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያግዝ ሲሆን ማዕከሉ እውን እንዲሆን ትልቁን ድርሻ የተወጣችውን አርቲስት አለምጸሃይ ወዳጆን ላመሰግናት እወዳለሁ።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review