በለውጡ ዓመታት በማህበራዊ ዘርፍ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
ለተመዘገቡት ስኬቶች በርካታ መሠረቶች የነበሩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን እምቅ አቅም ለመለየት እና ለመጠቀም በፓርቲው ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንቶች በሳል አመራር ሰጪነት የተደረገው ርብርብ ተጠቃሽ ነው።
ብልፅግና ፓርቲ በ2ኛ መደበኛ ጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን የፓርቲው ፕሬዚዳንት አድርጎ መርጧል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሆነው ተመርጠዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት እንደሀገር ያጋጠሙትን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ተቋቁሞ በሁሉም መስክ አመርቂ ውጤቶች በማስመዝገብ ቃሉን በተግባር መግለጥ የቻለ ፓርቲ ነው፡፡
ፓርቲው በመጀመሪያ ጉባኤው “የመነሳት” ምዕራፍ በሚል በሰየመው ዘመን ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች እና ለማከናወን ቃል የገባቸውን ተግባራት በመፈፀም ስኬታማ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
በዚህም በሀገር በቀል እሳቤ ሁለንተናዊ ብልጽግና የተረጋገጠባት ኢትዮጵያ ዕውን በመሆን ላይ ትገኛለች።
ለጥራት፣ ለፍጥነት እና ለፈጠራ ትኩረት ሰጥቶ መሠራቱ፣ ከብዝሀ የኢኮኖሚ ዘርፎች አኳያ በግብርና፣ በቱሪዝም እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ተጨባጭ ስኬቶች የተመዘገቡባቸው ሲሆን፣ በማህበራዊ ዘርፍም ባለፉት ዓመታት በተለይም በሰው ተኮር ስራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሰሩ ሥራዎች ለተገኘው ውጤት ተጨማሪ አቅሞች ሆነዋል።
ከ2010 በተደረገው ሀገራዊ ለውጥ ቀደም ብለው የነበሩ ሦስት አስርት ዓመታት እና ከለውጡ ማግስት ያሉ ስድስት ዓመታት ሲነፃፀሩ፣ ከለውጡ በፊት ያሉ ዓመታት፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ተከታታይ የሚባል ልማት እና የኢኮኖሚ እድገት ( ባለ ሁለት አሃዝ እድገት የተባለለት ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት) አስመዝግባለች፡፡
ይሄ እድገት ግን አንደኛ የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል፣ ሁለተኛ የዜጎችን የስራ ዕድል ፈጠራ እና ተጠቃሚነት እውን በማድረግ፤ እንዲሁም ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ በኩል ይሄ ነው የሚባል አስተዋፅዖ አልነበረውም፡፡ ምክንያቱም፣ ልማትና ሰው ሳይገናኙ፤ ልማቱ ሰው እንዳሳደደ፣ ሰውም ከልማቱ እንዲሸሽ እየተደረገ የኖረበት ነበርና፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በትምህርት፣ በጤና፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን በማቃለል፣ የኮሪደር ልማትን በመጀመር የብልጽግና ትልሞች እና ግቦች በተሻለ ውጤት እንዲጓዙ ተደርጓል።
በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ክልሎች እየተከናወኑ ያሉ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች የዜጎችን ህይወት በተጨባጭ የቀየሩ ናቸው።
በኮሪደር ልማት፣ በተማሪዎች ምገባ፣ አቅመ ደካሞችን እና አረጋውያንን ተጠቃሚ ያደረጉ ልማቶች የቤት እድሳት እና ምገባ የመሳሰሉት፣ የሴቶች እና የህጻናት ማሳደጊያ ማዕከላት ላይ የተከናወኑ ስራዎች ዜጎችን በተጨባጭ ተጠቃሚ አድርገዋል።
በእነዚህ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች በርካታ ዜጎችም የስራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል።
ለዚህ ስራ መሳካት የፓርቲው ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የላቀ ሚና ነበራቸው።
በዚህ የፓርቲው 2ኛ መደበኛ ጉባኤ እና “የማንሰራራት” ምዕራፍ በሚል በተሰየመው ቀጣይ ዘመን፣ ፓርቲው ለሕዝብ የገባውን ቃል በተግባር ሙሉ ለሙሉ የሚፈጽምበት እንደሚሆን እና ህዝቡን አስተባብሮ በመሥራት ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል በመቀየር መጓዝ ይጠበቃል።
በታምራት ቢሻው