የሀገሪቱ መሠረታዊ ችግሮች እንዲፈቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

You are currently viewing የሀገሪቱ መሠረታዊ ችግሮች እንዲፈቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

AMN-ጥቅምት 20/2017 ዓ.ም

በዕውቀትና እውነት ላይ በመመስረት የሀገሪቱን መሠረታዊ ችግሮች እንዲፈቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚናቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስገነዘቡ።

ሚኒስትሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመማር ማስተማርና ምርምር ስራዎች የሀገሪቱን የልማትና የለውጥ ጉዞ ለማሳካት በሚኖራቸው ሚና ዙሪያ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

በዚህ ወቅት ሚኒስትሩ እንዳመለከቱት፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዜጎች በነፃነት የሚማሩባቸውና የሚመራመሩባቸው መድረኮች ናቸው።

ይህንን ተግባር በአግባቡ በማስፈጸም በዕውቀትና እውነት ላይ ተመስርተው የሀገሪቱን መሠረታዊ ችግሮች እንዲፈቱ የሚያደርጉትን ጥረት ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

እንዲሁም ተቋማቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ችግር ፈቺ ውይይትን በማጠናከር መልካም አስተዳደር ማስፈን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ተቋማቱ በያሉበት አካባቢ ያሉ ፀጋዎችን በመለየት ማህበረሰቡን በተጨባጭ የሚቀይር ምርምርና ጥናት ማድረግም እንዲሁ።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማር ሥራ ባለፈ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች በመሠረታዊነት በመፍታት ካደጉ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይገባል።

መንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የሚመዝነው የተቋቋመለትን ዓላማ በአግባቡ በመፈጸም የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አንጻር እንደሆነ አብራርተዋል።

በውይይቱ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አመራር አባላት፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን፤ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review