AMN-መስከረም 20/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ ግንቦት ወር ላይ የተጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብና ለምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮች ልየታ ሂደት በተለያዩ ክልሎች እየተካሄደ ይገኛል።
እስካሁንም ምክክር ኮሚሽኑ በ5 ክልሎችና በ2 ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብና ለዋናው የምክክር ጎባኤ የሚሳተፉ የተወካዮች ልየታ አካሂዷል።
ከነገ ጀምሮ እስከ መስከረም 27 2017 ዓ.ም ደግሞ በአፋር ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራን ያከናውናል።
የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ የሰጡት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባሳደር ዶ/ር አይሮሪት መሐመድ፣ በክልሉ የጎሳ መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ከ9 የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ እና ከ49 ወረዳዎች የተወጣጡ ከ800 በላይ ተሳታፊዎች አጀንዳቸውን ያቀርባሉ ብለዋል።
ከ700 በላይ የሚሆኑ እንደ ፖለቲካ ፖርቲዎች፣ ተቋማት፣ ማህበራትን የመሳሰሉ ባለድርሻ አካላትም በዚሁ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተወካዮች ልየታ እንደሚሳተፉ ነው ኮሚሽነሯ የተናገሩት።
በዚሁ የምክክር ምዕራፍ መድረክ የሚሳተፉ ወኪሎች ሀገራዊ ጉዳዮችን የያዙ አጀንዳዎችን በማንሳት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ኮሚሽነሯ አስገንዝበዋል።
የምክክር መድረኩን የሚመሩና የሚያስተባብሩ የኮሚሽኑ የባለሙያዎች ቡድንም ሰመራ ከተማ ተገኝተው ቅድመ ዝግጅት አጠናቅቀዋል።
በፍቃዱ መለሰ