AMN – ታኅሣሥ 20/2017 ዓ.ም
መንግሥት ለሰላም እጁን የመዘርጋቱን ያህል ህዝብና ሀገር ለማወክ የሚሞክሩ ኃይሎችን ስርዓት የሚያስይዙና ህግ የሚያስከብሩ ጠንካራ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት መገንባቱን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
መንግሥት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት ከታጠቁ ቡድኖች ጋር ያደረጋቸው ውይይቶች ፍሬያማ መሆናቸውን አውስተዋል።
የሰላም ዋና ምንጭ ልማት፣ የህዝብ ተጠቃሚነትና የስራ ዕድል መፍጠር መሆኑን ያነሱት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፥ በዚህም ብሶት የሚፈጥሩ ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል ብለዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት በአስተዋይነት ለሰላማዊ አማራጭ በር በመክፈት ጥሪ ማቅረቡን አውስተዋል።
በዚሀም በትግራይ ክልል የነበረው ችግር በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መቋጨቱን ተናግረዋል።
በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከሚንቀሰቀሱ ታጣቂዎች ጋር የሰላም ንግግሮች መጀመራቸውን በመጥቀስ ጥረቱ ፍሬ እያፈራ፣ የታጠቁ ቡድኖችም ወደ ሰላም እየመጡ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ካላት ገናና ታሪክ አንጻር ባለፉት አስርት ዓመታት ያለፈችበት መንገድ አስከፊ በመሆኑ ይህንን ለመጨረሻ ጊዜ መዝጋት እንደሚገባም ነው ያነሱት።
የሀገሪቱን የሰላምና የፖለቲካ ድባብ ለመቀየር የሽግግር ፍትሕና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወደ ተግባር መግባታቸውን ጠቅሰዋል።
የልዩነት አጀንዳ ያላቸው ሁሉ በአንድ ላይ በመምከር ችግሮችን መፍታትና ለተሻለ የሀገር ግንባታ በጋራ አዲስ መንገድ መቅረፅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሰላምን በፈቃድ ብቻ ስለማይመጣ ህግ የሚያስከብሩ ጠንካራ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት መገንባታቸውንም አንስተዋል።
ተቋማቱ የህዝብና የሀገር ደህንነትን ማስጠበቅ ላይ በጠንካራ ቁመና እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም አፈንጋጮችን ወደ መስመር ለማስገባት ያስችላል ያሉት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፥ በቀጣይም ሰላምን የማፅናትና ሀገርን ከግጭት ጠማቂዎች የመጠበቅ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ግጭትን እንደ ገቢ ማስገኛ የሚጠቀሙ አካላት፣ ማህበራዊ ሚዲያን ለጥላቻ የሚያውሉ እና የውጭ ሃይሎች ኢትዮጵያ ህልሟን እንዳታሳካ የተለያዩ ሙከራዎችን ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ፈተናዎችን በመቋቋም ሀገርን ቀና የሚያደርጉ የልማትና የሰላም ስኬቶች መመዝገባቸውን በማሳያነት ጠቅሰው ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ደፋርና ብስለት የተሞላበት ሰላማዊ አማራጭን እየተከተለች መሆኗን ጠቅሰዋል።
በዙሪያዋ ከሚገኙ ሀገራት ጋር ሰላማዊ ጉርብትናን እና የልማት ትብብርን ለማጎልበት በቀዳሚነት እየሠራች እንደምትገኝም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡