የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የዲፕሎማሲ መምሪያ ሰነድ ይፋ ተደረገ

You are currently viewing የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የዲፕሎማሲ መምሪያ ሰነድ ይፋ ተደረገ

AMN- ሰኔ 02/2017 ዓ.ም

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ እና ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የዲፕሎማሲ መምሪያ ሰነድ ዛሬ ይፋ ተደርጓል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ ያለውን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የፈጠረውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በውል ተገንዝቦ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸው፣ የዲፕሎማሲ መምሪያ ሰነዱ ዲፕሎማቶች ለውጦችን በጥልቀት ተገንዝበው ሥራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በዲፕሎማሲ ሥራችን መሠረታዊ የቅኝት ለውጥ እያመጣን መሆኑን እና ያም የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ ያተኮረ ለመሆኑ የዛሬው ሰነድ አንድ ማሳያ ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ በበኩላቸው፣ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የዲፕሎማሲ መምሪያ እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦችን እና የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችን ለውጭ ዓለም ለማስተዋወቅ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

መንግሥት ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ዲፕሎማቶች የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በማስተዋወቅ የውጭ ኩባንያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለመሳብ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review