AMN-መስከረም 27/2017 ዓ.ም
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ይካሔዳል፡፡
በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 58 ንዑስ አንቀፅ (2) እና በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት የሥነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀፅ 24 ንዑስ አንቀፅ (1) መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንድ ዓመት የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ መሆኑ ተደንግጓል፡፡
በድንጋጌው መሰረት የ6ኛው ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የተጠናቀቀ ሲሆን 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓትም የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት በተገኙበት ዛሬ ከቀኑ 8 ሠዓት ጀምሮ ይካሄዳል ተብሏል፡፡
በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይም የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት ለሁለቱ የፌዴራል መንግሥት ምክር ቤቶች ዓመታዊ ሥራቸውን መጀመራቸውን በማብሰር የፌዴራል መንግሥቱን ዓመታዊ ዕቅድ ያቀርባሉ።
የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደሚገኙም ተጠቁሟል፡፡