የሄፓታይተስ “ሲ” መንስኤው፣ ምልክቶች እና መከላከያው

You are currently viewing የሄፓታይተስ “ሲ” መንስኤው፣ ምልክቶች እና መከላከያው
  • Post category:ጤና

AMN- ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም

ሄፓታይተስ “ሲ” በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት ኢንፌክሽን ሲሆን የጉበት እብጠት የሚያስከትል በሽታ ነው፡፡ ይህ በሽታ ለብዙ ጊዜ ምንም አይነት ምልክት ሳያሳይ የሚቆይ በመሆኑ ከባድ የጉበት ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የማዮ ክሊኒክ የጤና መረጃ ያመላክታል፡፡

መተላለፊያው፡-

ሄፓታይተስ “ሲ” ቫይረስ በዋነኝነት የሚተላለፈው በተበከለ ደም ንክኪ አማካኝነት ሲሆን ደህንነቱ ባልተጠበቀ መርፌ(ክትባት) እና ጥንቃቄ በጎደለው የግብረ ስጋ ግብኙነትም ሊከሰት እንደሚችልም ነው የጤና መረጃው የሚያመለክተው፡፡

የሚያሳቸው ምልክቶች፡-

የሄፓታይተስ “ሲ” ኢንፌክሽን ምልክት ሳያሳይ ለብዙ ጊዜያት የሚቆይ ቢሆንም በሽታው ሲጀምር ግን አጣዳፊ በሆነ ሁኔታ እንደሆነ የጤና መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ከሚያሳያቸው ምልክቶች መካከል፡-

የሰውነት መገርጣት፣

ድካም፣

ማቅለሽለሽ፣

ትኩሳት እና የጡንቻ ሕመም ይጠቀሳሉ፡፡

ሄፓታይተስ “ሲ” ቫይረስ ለረጅም ጊዜ ሲቆይ ሥር ወደ ሰደደ ሄፓታይተስ “ሲ” ሊቀየር ይችላል፡፡

ስር የሰደደ የሄፓታይተስ “ሲ” የሚያሳያቸው ምልክቶች የሚከሰቱት ቫይረሱ ጉበትን በከፍተኛ ሁኔታ ከጎዳ በኋላ ሲሆን የሚከተሉትን ምልክቶችም ያሳያል፡፡

በቀላሉ ደም መፍሰስ፣ ድካም፣ መብላት አለመፈለግ፣ የቆዳ ቀለም ቢጫ መሆን፣ የአይን ነጩ ክፍል ወደ ቢጫነት መለወጥ፣ የሽንት መጥቆር፣ የቆዳ ማሳከክ፣ በጨጓራ ውስጥ ፈሳሽ መከማቸት፣ በእግር ላይ እብጠት መከሰት፣ ክብደት መቀነስ፣ ግራ መጋባት፣ ድብታ እና የደበዘዘ ስሜት መኖር፣ በቆዳ ላይ የሸረሪት ምስል የሚመስሉ የደም ስሮች መታየት እና ሌሎችም ምልክቶች ይጠቀሳሉ፡፡

መከላከያው፡-

የሄፓታይተስ “ሲ” ኢንፌክሽንን ለመከላከል አስፈላጊውን የጤና ምርመራ ማድረግ እና ከተበከለ ደም ንክኪ መራቅ ዋነኛ መከላከያው ሲሆን ጥንቃቄ ከጎደለው የግብረ ስጋ ግንኙነት መቆጠብም በባለሙያዎች ይመከራል፡፡

ብዙውን ጊዜ የሄፓታይተስ “ሲ” ኢንፌክሽን ምልክቶች በቀላሉና በቶሎው ስለማይታዩ ብዙ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ላያውቁ ይችላሉ፡፡

ስለዚህ በቫይረሱ አማካኝነት የሚከሰትን የረጅም ጊዜ የጉበት ጉዳት እና መሰል ችግሮችን ለመከላከል ቀድሞ በመመርመር አስፈላጊውን ህክምና ማግኘት ተገቢ መሆኑን የማዮ ክሊኒክ የጤና መረጃ ያስገነዝባል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review