AMN-መስከረም 21/2017 ዓ.ም
ሄፓታይተስ “ቢ” በአብዛኛው በጉበት ላይ የሚከሰት የቫይረስ ኢንፌክሽን ሲሆን፤ በሄፓታይተስ “ቢ” ቫይረስ (HBV)አማካኝነት የሚመጣ ነው።
ይህ ኢንፌክሽን የአጭር እና የረዥም ጊዜ የጉበት በሽታን ሊያስከትል እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ከተለመዱት ከባድ የጉበት ኢንፌክሽኖች መካከል አንዱ እንደሆነ በጤና ባለሙያዎች የሚነገርለት ይህ ኢንፌክሽን፣ በዓለም ወደ ሁለት ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ መረጃዎች ያመላከታሉ፡፡
ሄፓታይተስ “ቢ” የሚተላለፍባቸው መንገዶች፡-
ሄፓታይተስ “ቢ” በተለያዩ መንገዶች ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል፡፡
ከእነዚህም መካከል፡- በወሊድ ወቅት ከእናት ወደ ልጅ ፣ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት በሚፈጽምበት ጊዜ፣ ከደም ወይም ከሌሎች የሰውነት ፈሳሾች ጋር በሚደረግ ንክኪ፣ ደህንነቱ ያልተጠበቀ መርፌ ወይም ስለታም ለሆኑ መሳሪያዎች መጋለጥ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
ምልክቶቹም፡- ብዙ ሰዎች በሂፓታይተስ “ቢ” በሽታ ሲያዙ ምንም አይነት ምልክት እንደማያሳዩ የጤና መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ሆኖም ግን አንዳንድ ሰዎች ደግሞ በዚሁ በሽታ ሲያዙ የሚከተሉትን ምልክቶች እንደሚያሳዩ የጤና መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
አንድ ሰው በሄፓታይተስ “ቢ” ቫይረስ ሲያዝ ከሚያሳያቸው ምልክቶች መካከል፡- የቆዳ እና የዓይን ቢጫ መሆን፣ የሽንት መጥቆር ፣ ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት ፣ማቅለሽለሽ ፣ ማስታወክ ፣ የሆድ ህመም ፣ የጉበት እብጠት እና የምግብ ፍላጎት ማጣት ምልክቶችን ሊያስከትል ይችላል፡፡
መከላከያው ወይም ህክምናው፡- የሄፓታይተስ “ቢ” ኢንፌክሽንን ለመከላከል ዋነኛው መንገድ ክትባት እንደሆነ በባለሙያዎች ዘንድ በስፋት ይነገራል፡፡
በመሆኑም በዚህ በሽታ ላለመያዝ ክትቫት በወቅቱ መውሰድ ተገቢነት እንዳለው ነው የጤና መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡
ህፃናት ከተወለዱ በኋላ በ24 ሰዓታት ውስጥ የሄፓታይተስ “ቢ” ክትባት መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡
ክትባቱ ቢያንስ ለ20 ዓመታት እና ምናልባትም እስከ ህይወት ዘመን ከሄፓታይተስ “ቢ” ኢንፌክሽን ሊከላከል እንደሚችል ነው የሚገለፀው፡፡
በተጨማሪም በሄፓታይተስ “ቢ”ቫይረስ የመያዝ ስጋትን ለመቀነስ የግብረ ስጋ ግንኙነት ሲያደርጉ ኮንዶም በመጠቀም እና የወሲብ አጋሮችን ቁጥር መቀነስ፣ ደህንነታቸው ባልተጠበቁ መርፌዎች ከመወጋት መቆጠብ፣ ከደም፣ ከሰውነት ፈሳሾች ወይም ከተበከሉ ነገሮች ጋር ከተገናኘ በኋላ እጅን በሳሙና እና በውሃ በደንብ መታጠብ እንደሚገባ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያስረዳል፡፡