AMN-ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 4ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጫና የሚቀንስና ካፒታሉን ከፍ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ አፅድቋል፡፡
የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የመንግስት ዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡
በማብራሪያቸውም የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱትን ብድር ባለመመለሳቸውና የብድር ወለዱም በጣም ከፍ በማለቱ በባንኩ ላይ ጫና መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡
ባንኩ የሀገሪቱ ዋነኛ ተቋም በመሆኑም 900 ቢሊየን ብሩ የመንግስት ዕዳ ሰነድ ሆኖ እንዲከፈል እና መነሻ ካፒታሉም ከፍ እንዲል ውሳኔ ላይ መድረሱን አስረድተዋል፡፡
ስለሆነም ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁ በቀጥታ ወደ ሁለተኛ ንባብ ተሸጋግሮና ውይይት ተደርጎበት እንዲፀድቅ ጠይቀዋል፡፡
ምክር ቤቱ የቀረበውን ሞሽን የደገፈ ሲሆን፤ በቀጣይ በልማት ድርጅቶች በኩል ያለው አሰራር እንዲፈተሽ በምክር ቤት አባላት ጥያቄና አስተያየት ተሰጥቷል፡፡
ሞሽኑን አስመልክቶ ለቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች የገንዘብ ሚንስትሩ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ የልማት ባንኮች እና የልማት ድርጅቶች ምን አይነት ኪሳራ ላይ ወድቀው እንደነበር ይታወቃል ያሉት ሚንስትሩ፤ መንግስት ‹‹ከዕዳ ወደ ምንዳ›› የሚለውን መሪ ሀሳብ መሰረት በማድረግ በሰራው ማሻሻያ በርካታ የልማት ድርጅቶች ከኪሰራ ወደ ትርፋማነት እየተቀየሩ መምጣታቸውን አብራርተዋል፡፡
በቀጣይም በልማት ድርጅቶች ላይ የተሻለ ቁጥጥርና ድጋፍ እንደሚደረግም መጠቆማቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በመንግስት በኩል የተወሰደው እርምጃ በመንግስት ላይ የተወሰነ ጫና የሚያመጣ ቢሆንም ሊደርስ ከሚችለው ከፍተኛ ጉዳት ግን የታደገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ የመንግስት ዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1346/2017 ሆኖ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አፅድቆታል፡፡