AMN – ጥቅምት 19/2017 ዓ.ም
የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን እና ተወዳዳሪ የሆነ አገልግሎቶችን እንዲያቀርብ መንግስት አስቻይ የሆኑ የማበረታቻ ስልቶችን መዘርጋቱን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የኢፌዲሪ ቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ከሆቴል ፌዴሬሽኖች እና ከቱሪዝም የሙያ ማህበራት ኃላፊዎች እና ተወካዮች ጋር በቅንጅት መስራት በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይታቸው የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን እና ተወዳዳሪ የሆነ አገልግሎቶችን እንዲያቀርብ መንግስት አስቻይ የሆኑ የማበረታቻ ስልቶችን መዘርጋቱን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በጥምረት በመስራት፤ የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል መወያየት ዘርፉ የተጣለበትን ሀገራዊ ፋይዳ እንዲያበረክት ወሳኝ መሆናቸውን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡
የማህበራቱ ተወካዮቹ በበኩላቸው መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት አድንቀው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም የቱሪዝም ሳተላይት አካውንትን በማስጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
ተወካዮች በዘርፉ አሉብን ያሏቸውን ከደረጃ ምደባ፣ ከእሳት አደጋ መከላከል፣ ከቀረጥ ነጻ ፈቃድ እና መሰል ችግሮች ያነሱ ሲሆን ሚኒስትሯ በቀጣይ በአጭር ፣በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ የሚፈቱበትን አግባብ እና የግንኙነት ጊዜ በተመለከተ አቅጣጫ መስጠታቸውን ከቱሪዝም ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል።