AMN – ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም
የለዉጡ መንግስት ሀገሪቱን መምራት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የከተማዋን ልማትና ሰላም በመጠበቅ ረገድ በርካታ ድሎችን ማስመዝገብ ተችሏል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ገለጹ፡፡
“ሃገር ወዳድነት እና ሰላም ግንባታ”በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው ከተማ አቀፍ የሠላም ኮንፈረንስ ተጠናቋል፡፡
በኮንፍረንሱ ላይ የአገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩ አንዳንድ አካላት እንዳሉ የሚታወቅ ነው ሲሉ ኃላፊዋ ገልጸው በአንፃሩ ደግሞ በቅርቡ የሰላም ጥሪውን በመቀበል ወደ ህብረተሰቡ የተቀላቀሉ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁንም ቀሪ አካላት የሰላም ጥሪውን መቀበሉ ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ሰላምና ዕድገት የሚበጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት በማድረግና በተፈጠሩት አደረጃጀቶች የአካባቢንም ብሎም የሀገርን ሰላም ማስጠበቅ ይገባል ያሉት ኃላፊዋ የልማት ስራዎችን በተቀመጠላቸው ልክ ለማጠናቀቅ ሰላም መከበር ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በቀጣይም በከተማዋ ላይ በርካታ የአደባባይ በዓላት የሚከበሩ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ም/ቢሮ ሀላፊ አቶ ተስፋዬ ጫኔ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለከተማው ሰላም ጠንክሮ መስራት እንደሚገባው ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የብልግና ፖርቲ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አብረሃም ታደሰ በበኩላቸው የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ ህብረተሰቡ ለሰላም በከፈለው ዋጋ የተመዘገቡ ዉጤቶችን ዘላቂ ማድረግ ይገባል ብለዋል ።
“ሀገር ወዳድነትና የሰላም ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በመጨረሻም ኮንፈረንሱ ባለ አራት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማዉጣት መጠናቀቁን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡