ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች ዋነኛ ተግባራቸው ህይወትን መሄስ ነው፡፡ ሕይወትን በተለያየ መልኩ የመተርጎም ተግባርን ይከውናሉ። ያልታየውን በማሳየት፤ የደበዘዘውን በማጉላት የፈጠራ ሥራዎች አግራሞትን በተደራስያን ላይ ይፈጥራሉ፡፡ ታዲያ ስለ ኪነ ጥበብ ሥራ ስንጨዋወት ከያኒውም አብሮ ይመጣል፡፡
ከያኒው ለምንድን ነው የሚከይነው? ለመከየን የሚያነሳሳው ገፊ ምክንያትም ምንድነው? ሕይወትን በገባውና በተረዳው ልክ ለመሄስ ምን ያህል ትጋት አለው? የከያኒው ሃቀኝነቱስ እስከምን ድረስ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም ደርዝ ያለው የኪነ ጥበብ ሥራ ያለ ኹነኛ ከያኒ ማሰብ አዳጋች ስለሆነ፡፡ እኛም በዚህ ዓምድ ላይ ለብዙ የሃገራችን የኪነ ጥበብ ሰዎች አብነት ሊሆን የሚችለው ደራሲና ተርጓሚ ሌሊሳ ግርማን በጨረፍታ ልናስቃኛችሁ ወድደናል። በዚህ አጭር ጽሑፍ ግን የሌሊሳን ሁሉንም የድርሰት ሥራዎች ሳይሆን በዋናነት በቅርቡ ለንባብ በበቃው የትርጉም ስራውና የድርሰት ዳናዎቹ ላይ ነው አጭር ቅኝት ለማድረግ የመረጥነው፡፡
ሌሊሳን በዛሬና በትናንት መካከል
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታተሙ ጋዜጣዎችና መጽሔቶችን የማንበብ የዓመታት ልምድ ያለው ሰው ሌሊሳ ግርማ እንግዳ ሊሆንበት አይችልም። ለዓመታት በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ላይ ሌሊሳ ውብ የሆኑ አጫጭር ልብወለዶችና ኢ-ልብወለድ መጣጥፎችን አስነብቦናል፡፡
የተለያዩ ፍልስፍናዊና ማህበራዊ ሂሶችን በመጻፍ ያላስተዋልነውን እንድናስተውል፤ ችላ ያልነውን እንድናስታውስ በስራዎቹ ቀስቅሶናል። ያለማቋረጥ ላለፉት ሃያ ዓመታት ገደማ ሌሊሳ በርካታ ድንቅ የፈጠራና ፍልስፍናዊ ዕሳቤዎቹን አጋርቶናል። ለዚህ ነው ለጋዜጦችና መጽሄቶች ቅርበት ላለው ሰው ሌሊሳ ግርማ እንግዳ የማይሆነው፡፡ ምክንያቱም እሱ ከትናንት እስከ ዛሬ በኪነ ጥበብ መድረኮች ላይ ዳናውን ትቷልና። እዚህ’ጋ የራሴን ልምድ እንደ አብነት ልጥቀስ፡፡ በተለያዩ ቀናት የሚታተሙ ጋዜጣዎችና መጽሄቶችን የማንበብ የቆየ ዝንባሌ አለኝ፡፡ ጋዜጣዎችና መጽሄቶች ተከራይቶ ከማንበብ እስከ ገዝቶ ማንበብ የዘለቀ ዝንባሌ። ታዲያ ይታተሙ የነበሩ ጋዜጣዎችና መጽሔቶች ላይ አንድ ሰው ከጻፈ በፍጹም መተው አልችልም ነበር፡፡ መጀመሪያ የማነበውም የእሱን ጽሑፍ ነበር፡፡ አሁን ላይ አልፎ አልፎ ቢሆንም ይህ ሰው ከጻፈ መጀመሪያ የማነበው የእሱን ጽሑፍ ነው። ይህ ሰው ደግሞ ሌሊሳ ግርማ ነው፡፡
ዘግይቼም ቢሆን የሌሊሳን አጫጭር ልብወለዶች፣ ፍልስፍናዊ እሳቤዎቹን የያዙ መጣጥፎችና ማህበራዊ ሂሶቹን በተለየ ትኩረት እንዳነባቸው ዋነኛ ምክንያቴ የሚያነሳቸው ሃሳቦች በጣም ጥልቀት ስላላቸው ነው። ያለማጋነን የሌሊሳ ጽሑፎች የ‘አዕምሮ ጂምናስቲክ’ ያሰራሉ። ያመራምራሉ፡፡ አንስቶ የሚጥላቸው ሃሳቦች በተደራሲያን ላይ በቀላሉ ይጋባሉ። እንዴ…?! በማስባል አግራሞትን ያጭራሉ። አንድን ጉዳይ ባልተረዳነው መንገድ ገልጦ በማሳየት ጉድ! ጉድ!…ያስብላሉ፡፡ በአጭሩ ሌሊሴ ጥልቅ የሆኑ የህይወት ጥያቄዎችን ኪናዊ በሆነ መንገድ አጉልቶ የሚያሳይ ደራሲ በመሆኑ በሚያውቁትና ባነበቡት ሰዎች ዘንድ እንዲወደድ አድርጎታል፡፡
ደራሲ እሱባለው ንጉሴ የዛሬ ዓመት ገደማ “ቃላት” በተሰኘው ኪናዊ የዲጂታል መጽሔት ላይ ስለ ሌሊሳ ደራሲነትና ስራዎች ካሰፈረው ትንታኔ ትንሽ መስመሮች እነሆ፤ “ሌሊሳ ከነባሩ ሀገራዊ የሥነ-ጽሑፍ ልማድ መልካቸውን ባልቀዱ ኤክስፐርመንታልና ረቂቅ ልብ ወለዳዊና ኢ-ልብ ወለዳዊ ሥራዎቹ ደፋርና የተሳካ ኪናዊ ፍንገጣን ያደረገ ብርቱ ደራሲ ነው። አታካችና ቅብ መደበኛ ጌጦችን አራግፎ በሃቀኛ ዕርቃኑ የጠራ የመንገር አቅምን የተጎናጸፈ ብስል ቋንቋው፣ ረቂቅ ምናብና ጥልቅ እሳቤን በማዋቀር ያዋለደው የራሱ ልዩ ሥነ-ጽሑፋዊ ቅርጽና የሚያነሣቸውን አንኳር ነገሮች መልክ በጠለለ ፍልስፍናዊ አተያይ አጥርቶ የሚፈትሽበት የከያኒ ተአማኒነቱ እጅግ የላቀ ነው…” እያለ ይቀጥላል፤ በዚህ አቀራረቡ ሌሊሳን ጥሩ አድርጎ ሊገልጸው ሞክሯል፡፡ ያለማጋነን ብዙዎችን የሚያስማማ ገለፃ ነው፡፡
ሌሊሳ በጋዜጣዎችና መጽሄቶች ላይ የፃፋቸውን ጽሑፎች አክሎ ያሳተማቸው የተለያዩ ኪናዊ ስራዎቹ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ትልቅ ገጸ-በረከት ናቸው፡፡ የሌሊሳ ዳናዎች ጭምር። “አፍሮጋዳ”፣ “የንፋስ ህልም”፣ “እስቲ ሙዚቃ”፣ “መሬት – አየር – ሰማይ”፣ “የሰከረ እውነታ”፣ “ነፀብራቅ” እና “ይመስላል ዘላለም” ሌሊሳ ለንባብ ያበቃቸው ተወዳጅ የድርሰት ሥራዎቹ ናቸው። እንዲሁም ከሌሎች ጸሐፊያን ጋር በጋራ ከተሳተፈባቸው ሥራዎች መካከል “መልክአ ስብሐት”፣ “አማሌሌ”፣ “አልፋ ተረክ”፣ “Addis Ababa Noir”፣ “ጉራማይሌ” ይጠቀሳሉ። አሁን በቅርቡ ለንባብ ያበቃው “ደማቆቹ” መጽሃፍ ግን ከሌሎቹ በመጠኑ ይለያል፡፡ የዓለማችን ምርጥና ዕውቅ ደራሲያን የአጫጭር ልብወለድ ሥራዎችን ተርጉሞ ነው ለንባብ ያበቃው፡፡
የትርጉም ሥራዎችን በጨረፍታ
ለአንድ ሃገር የሥነ ጽሑፍ ዕድገት ጉልህ ሚና ከሚጫወቱ ነገሮች አንዱ ነው፤የትርጉም ስራ። በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ መጻሕፍት ወደ ሃገርኛ ቋንቋ መተርጎም አንድም ቋንቋን ለማጎልበት፤ አንድም ተደራሲያን በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ አውታረ-ብዙ መረዳትን እንዲያዳብሩ ያስችላል። የተለያዩ ማህበረሰቦች የህይወት ዘይቤያቸውና ፍልስፍናቸው፤ ውድቀታቸውና እድገታቸው፤ እንዲሁም ያለፉበትን ውስብስብ የታሪክ ሂደትና አንድምታው ለመረዳትም የትርጉም ስራዎች ፋይዳቸው በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ በእነዚህ የትርጉም ስራዎች አማካይነት ሃገራዊ አውድን ባገናዘበ መንገድ ለመማርና ጉድለትን ለመሙላት ሁነኛ ምንጮች ናቸውና፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በውጭ ቋንቋዎች የተጻፉ ኪናዊ የፈጠራ ስራዎችን ወደ አማርኛ በመተርጎም በኩል ከ1940 ዓ.ም ወዲህ ቀስ በቀስ እያደገ መጥቷል፡፡ በዚህ በኩል ኪናዊ የፈጠራ ስራዎችን በመተርጎም ረገድ ባለቅኔና ተርጓሚ ከበደ ሚካኤል ቀዳሚው ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለአብነትም ከበደ ሚካኤል የሼክስፒርን ሮሚዮና ጁሌት በ1940ዎቹና ሌሎች አጫጭር ታሪኮችን በመተርጎም በፈር-ቀዳጅነት አስተዋጽኦው የጎላ ነው ፡፡ በ1950ዎቹ መጨረሻና በ1960ዎቹ ደግሞ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን በርካታ የሼክስፒር ስራዎችን ወደ አማርኛ ቋንቋ ተርጉሟል። ለአብነትም ኦቴሎና ማክቤዝ ከተረጎማቸው የፈጠራ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት የአማርኛ የትርጉም ስራዎች በከፍተኛ ደረጃ የጨመሩት ግን ከ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ማግስት ጀምሮ ነው። በተለይ በአብዮቱ ማግስት የተቋቋመው የ“ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት” ለትርጉም ስራዎች መበራከት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ገጣሚና መምህር በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)፣ ”ትርጉም ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ያበረከተው አስተዋጽኦ ቅኝት” በሚለው ጥናታቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
በተለይ በሩሲያ ቋንቋ የተጻፉ ዘመን አይሽሬ የፈጠራ ስራዎችን በአማርኛ ቋንቋ እንዲተረጎሙ የዘመኑ ሁኔታ ምቹ አጋጣሚን ፈጥሯል፡፡ ለአብነትም የዕውቁ ሩሲያዊ ደራሲ የፊዮዶር ዶስቶቭስኪ “Crime and Punishment”ን “ወንጀልና ቅጣት”፣በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተተርጉሟል። የሌላኛው ሩሲያዊ ደራሲ የማክሲም ጎርኪ “My Universities” የተሰኙ መጻህፍት በሶስት ቅጾች “ዩኒቨርስቲዎቼ”፣ እንዲሁም የአንቶን ቼኾቭና ኒኮላይ ጎጎል ስራዎች ወደ አማርኛ ተተርጉመው ለንባብ በቅተዋል፡፡ ታዲያ የእነዚህ እውቅ ደራሲያን ስራዎች በላቀ ጥራትና ኪናዊ ፋይዳ በሃገርኛ ቋንቋ መተርጎማቸው ለብዙሃኑ በቀላል መንገድ ተነብበው ለመወደድ በቅተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን በላቀ ብቃት በመተርጎም ደረሲና ተርጓሚ ሳህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም፣ ተርጓሚ መስፍን አለማየሁና ገጣሚና ጋዜጠኛ ነቢይ መኮንን ትልቅ ባለውለታችን ናቸው፡፡ ሌሊሳም ንባቡ ሰፊ፣ መረዳቱ ጥልቅ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመጻፍም ሆነ በመተርጎም ችሎታው ጥያቄ የማይነሳበት ደራሲ ነው፡፡ አሁን ለንባብ ባበቃው የአጫጭር ልብወለዶች የትርጉም ሥራው፣ ከእነዚህ አንጋፋ ተርጓሚዎች ተርታ ብናስቀምጠው ድፍረት አይሆንብንም፡፡ ምክንያቱም አጫጭር ልብወለዶቹ ቋንቋን በመቻል ብቻ ተነሳስቶ እንዳልተረጎማቸው ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ እንችላለን፡፡
ሌሊሳ የተረጎማቸው እነዚህን አጫጭር ልብወለዶች ስናነባቸው ተረኮቹ ስሜታችንን ቆንጥጠው የመያዝ ትልቅ አቅም አላቸው፡፡ ስናነባቸው የትርጉም ሥራ መሆናቸው ብዙም አይታወሰንም፡፡ ሌሊሳ የራሱን የፈጠራ ክሂልና ልምድ ተጠቅሞ ነው እነዚህን የሥነ ጽሑፍ የትርጉም ስራዎች ስብስብ የሆነው “ደማቆቹ”ን አድምቆና አስውቦ ያስነበበን፡፡
‘ደማቆቹ’ን በደማቁ ደራሲ
በዚህ መጽሐፍ መግቢያ ላይ ተርጓሚው ሌሊሳ እንዲህ ሲል ይጀምራል፤ ”አጭር ልብወለድ አንድን ገጠመኝ ብቻ የሚተርክ አይደለም። አፈ ታሪክ አውሪ፣ ገድል ዘካሪ፣ የሀገረ ሰብ ታሪክ ማሸጋገሪያ አይደለም።… የአንድን አጋጣሚ ምስል በግርድፉ ለመንገር የሚጠቅም ጽሑፋዊ ንድፍ አይደለም። የአንድ ሰው ግለ ታሪክ ወይንም የሀገር ታሪክ አጭር ልብ ወለድን አይወክልም። እንደ ‘አንድ ሺ አንድ ሌሊት’ አይነት ተረቶች መናገርም የአጭር ልብ ወለድ ልዩ መገለጫው አይደለም። እነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው ሁሉ ታሪክን ወይንም ተረክን ከሰው ወደ ሰው የማሸጋገሪያ፣ ራሳቸውን የቻሉ፣ የየራሳቸው ግብ ያላቸው መንገዶች ቢሆኑም፣ ዘመናዊ አጭር ልብ ወለድን በተለያየ መንገድ ዝርያው ሆነው ቢመስሉትም፣ሙሉ ለሙሉ አንደኛውም ሌላኛውን ነው ማለት አይቻልም” እያለ፤ የአጭር ልብወለድ ምንነትና ማተኮሪያ ምን እንደሚመስል ያብራራል፡፡
ሌሊሳ በዚህ መጽሃፉ መግቢያ ላይ የአጭር ልብወለድ ምንነት እንዲህ ማብራራቱን ይቀጥላል፤ “በአጋጣሚ አጭር ልብወለዱ ከላይ ከተዘረዘሩት መሃል አንደኛውን ተንተርሶ ወይንም ተወራርሶ ሊገኝ ይችላል፡፡ የእነዛኛዎቹ አላማ አንድ ከሆነ፣ የአጭር ልብወለድ ግን አሸን የግብ አማራጭ ሊኖረው ይችላል፡፡ ብዙ አማራጭን ሲጠቀልል የውበትነቱ ንጥረ ነገር ከፍ እያለ ይመጣል፡፡ ብዙ ዓላማ ያለውን ነገር በአንድ አላማ መጥራት የግድ ካስፈለገ አላማው ውበት ነው፡፡ የሁሉም ነገር መጠቅለያው ማዕቀፍ” በማለት ለውበት ልዩ አትኩሮት ይሰጣል፤ደራሲና ተርጓሚ ሌሊሳ ግርማ፡፡
ልክ እንደ ሰሎሞን ዴሬሳ፣ ሁሉ ሌሊሳ የኪነ ጥበብ ዋነኛ ተግባር ውበትን መፈንጠቅ ነው የሚል አተያይ ያለው ደራሲ ነው፡፡
ይሄ ፍልስፍናዊና ኪናዊ አተያዩን በተለያዩ አጋጣሚዎች ጽፏል፣ ተናግሯልም፡፡ በሌሊሳ ሥራዎች ውስጥም ይህ ኪናዊ አተያዩ ጎልቶ ይንጸባረቃል፡፡ በ”ደማቆቹ” የአጫጭር ልብወለድ የትርጉም ሥራዎች የተካተቱት የፈጠራ ሥራዎች ይህንን አተያይ መነሻ በማድረግ እንደተመረጡ አያጠራጥርም፡፡
ሌሊሳ በዚህ የአጫጭር ልብወለድ የትርጉም መጽሐፉ ካካተታቸው ዝነኛ ደራሲያን መካከል፣ ሶመርሴት ሞም፣ ሼርዉድ አንደርሰን፣ ፍራንክ አር እስቶክተን፣ ናጂብ ማህፉዝ፣ ፍራንዝ ካፍካ፣ ኧርነስት ሄሚንግዌይ፣ ገብርኤል ጋርሺያ ማርኩዌዝ፣ ማርጋሬት አትውድ፣ አንቷን ቼኮቭ፣ አየን ራንድን ጨምሮ የሌሎችም የዕውቅ ደራሲያን አጫጭር ልብወለዶች ተካቶበታል። እነዚህ የትርጉም ሥራዎች በተለይ በሃገርኛ ቋንቋ የተጻፉት ሥራዎችን ይበልጥ ለሚያነቡ ተደራሲያን ብቻ ሳይሆን በውጭ ቋንቋ የተጻፉትን ስራዎች ለሚያነቡ ተደራስያንም ጭምር ሊያነቡት የሚገባ ምርጥ የትርጉም ሥራ ነው፡፡
በአብርሃም ገብሬ