የሌማት ትሩፋቱ ሌላኛው ሰበዝ

You are currently viewing የሌማት ትሩፋቱ ሌላኛው ሰበዝ

በአዲስ አበባ ከተማ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር መተግበር ከጀመረ ወዲህ  ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ የከተማዋ ነዋሪዎች ከሸማችነት ወደ አምራችነት መሸጋገራቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ። ብዙዎች ከጓሮ አትክልት በተጨማሪ በእንስሳት ሀብት፣ በዶሮ እርባታ እና በእንቁላል ምርት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከራሳቸው አልፈው ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን ያሳደጉም አሉ፡፡ ይህም የከተማ ግብርና በትኩረት ከተሰራበት ውጤት ማምጣት እንደሚችል በተግባር አሳይቷል፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ነዋሪ የሆነው ወጣት ኤልያስ ፈሰስ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በዶሮ እርባታ ስራ ተሰማርቶ ይገኛል። በዘርፉ ውጤታማ ከሆኑ ወገኖችም አንዱ ሆኗል፡፡ በ30 እንቁላል ጣይ ዶሮዎች ስራውን የጀመረው ወጣቱ አሁን ከ600 በላይ እንቁላል ጣይ ዶሮዎች እንዳሉት ተናግሯል። ዱከም በመሄድ የዶሮ እርባታ ስልጠና ያገኘው ወጣት ኤልያስ ዘርፉ በፍላጎትና በትኩረት ከተሰራበት ውጤታማ የሚያደርግ ነው ይላል።

በርካቶች በሌማት ትሩፋት ማዕዳቸውን ሞልተው ለሌሎች መትረፍ ጀምረዋል

የመስሪያ ቦታ፣ የህክምና፣ የገበያ ትስስር እና የመኖ አቅርቦት በወረዳው የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት እንደተመቻቸለት የሚገልጸው ወጣቱ፣ በቀን ከ590 እስከ 600 እንቁላል እንደሚያገኝ ተናግሯል፡፡

ወጣት ኤልያስ እንደገለፀው፣ በወር ከእንቁላል ሽያጭ እስከ 30 ሺህ ብር ገቢ ያገኛል። የሌማት ትሩፋት የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር በማድረግ ረገድ እየተጫወተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ዶሮ በማርባት በእንቁላል ምርት የቤት ውስጥ ፍጆታን ከማሟላት አልፎ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል፡፡ በጥቅሉ የከተማ ግብርና በአግባቡ ከተሰራበት ውጤታማ ያደርጋል፡፡

ለሁለት ሰዎች የስራ እድል የፈጠረው ወጣቱ፣ የሌማት ትሩፋት ሁሉም በቤቱ ሰርቶ ተጠቃሚ የሚሆንበት የልማት ስራ እንደሆነ ጠቁሞ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ባላቸው ክፍት ቦታዎች ሁሉ ዶሮዎችን በቀላሉ በማርባት ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ይመክራል፡፡

በተመሳሳይ ወይዘሮ ሰላም ደበበ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በዶሮ እርባታ ስራ ተሰማርተዋል፡፡ ስራቸውን ከጀመሩ የቆዩ ቢሆንም በሌማት ትሩፋት በተጠናከረ መንገድ መስራት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ በ100 ዶሮዎች ስራውን ጀምረው አሁን 2 ሺህ እንቁላል ጣይ ዶሮዎች ያሏቸው ሲሆን፣ በቀን እስከ 1 ሺህ 500 እንቁላል ያገኛሉ፡፡

እንቁላል ወደ ገበያ በማውጣት ከሽያጩ የተሻለ ገቢ ማግኘት መቻላቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ ሰላም፣ ከተሰራ ውጤት ማግኘት ይቻላል ብለዋል፡፡ ሆኖም በዘርፉ የእንስሳት መኖ ዋጋ በየጊዜው የሚጨምር በመሆኑ ምክንያት ለመኖ መግዣ የሚያወጡት ወጪ ፈተና እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ሰላም አክለውም፣ ሰው ከሰራ የልፋቱን ውጤት ማግኘት ይችላል፡፡ በሌማት ትሩፋት ሁሉም በርትቶ በመስራት ከውጤቱ መቋደስ ይኖርበታል ሲሉ መክረዋል፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት የዶሮ እርባታ ባለሙያ አቶ በላቸው ንጉሴ የሌማት ትሩፋት ትግበራው በክፍለ ከተማው ውጤት ያመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፕሮግራሙ በዋናነት የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አንጻር በተለይ ከግብርና ምርት ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር በመሰረታዊነት መቅረፍ በሚችልበት ልክ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለው፣ በትግበራው በርካታ ውጤቶችም ታይተዋል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ በላቸው ገለጻ፣ ከዚህ ቀደም ትኩረት ሳይሰጠው የነበረውን የእንስሳት ዘርፉን በዋናነት ማዕከል በማድረግ ህብረተሰቡን ማሳተፍ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በቤተሰብ ደረጃ እያንዳንዱ ግለሰብ አምስት ዶሮዎችን በማርባት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ነው። በማዕድ ላይ የተመጣጠነ ምግብ እንዲኖር ለማድረግ ፕሮግራሙ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡

በክፍለ ከተማው 8 ሺህ 50 ነዋሪዎች በዶሮ እርባታ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ 50 ሺህ 145 የቄብ ዶሮዎች ለእነዚህ ወገኖች ተሰራጭቷል። በአመቱ 31 ሚሊዮን 380 ሺህ የእንቁላል ምርት መገኘቱን እና ለ4 ሺህ 536 ነባር ተጠቃሚዎች ድጋፍ በማድረግ ማጠናከር መቻሉን አቶ በላቸው ገልጸዋል፡፡ የሌማት ትሩፋት የእንቁላል የአቅርቦት እጥረትን እንዲሁም የዋጋ ሁኔታ የቀረፈ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የእንስሳት ሀብት ዳይሬክተር አቶ አሌክስ ደመቀ በከተማዋ ውስጥ እየተተገበረ ያለው የሌማት ትሩፋት ሥራ በስፋት ከመሰራቱ የተነሳ በከተማ ግብርና በተለይም በእንሰሳት ሀብት ልማት ሥራ ላይ የሚሳተፉ ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ አድጓል ብለዋል፡፡ በመሆኑም የዘርፉን ምርት እና ምርታማነት ማሳደግ ተችሏል። በመኖ አቅርቦት ላይ የሚስተዋለውን እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት ከባለሀብቶች ጋር ስምምነት ተፈርሟል፡፡ በምርት አቅርቦት ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ጫና በመቀነስ ሂደትም የራሱን ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ የሌማት ትሩፋት በምርት አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ይከሰት የነበረውን ክፍተት ለመሙላት የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ ማገዝ የቻለ ሲሆን፣  ለበርካታ ዜጎች ከደጃቸው በሚገኝ የግብርና ምርት ከራስ ፍጆታ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ችለዋል፡፡ በመሆኑም የግብርና ምርት አቅርቦት ለከተማዋ ነዋሪዎች በቅርበት በተለይም በተመረጡ የእሁድ ገበያዎችና በየአቅራቢያቸው ከሚገኙ የምርት አቅራቢዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ዕድል መፍጠሩን፤ በተለይ በበዓላት ሰሞን ይስተዋል የነበረውን የምርት እጥረት በማቃለል ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የኑሮ ውድነትን የማረጋጋት ሚናው እያደገ በመምጣቱ የእንቁላል ዋጋ ከ16 ብር ወደ 10 ብር በታች መውረዱ በመንግስትና በግል ተቋማት የተቀናጀና ዘመናዊ የግብርና ስራ መስፋፋት በመቻሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አቶ አሌክስ በከተማዋ በ2016 ዓ.ም 403 ሚሊዮን 74 ሺህ እንቁላል ለማምረት ታቅዶ፣ 556 ሚሊዮን 956 ሺህ ማምረት ተችሏል ብለዋል፡፡ በከተማ ደረጃ ያለው የእንቁላል ምርት በመጨመሩ በዋጋ እና በአቅርቦት ላይ በተለይም በበዓላት ወቅት ሊከሰት የሚችለውን የምርት ዋጋ ጭማሪ እና አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር ከፍተኛ ሚና ሊጫወት መቻሉን አቶ አሌክስ ገልጸዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ካለው ሀገራዊ ፋይዳ አንፃር እንደ ሀገር የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር እንደ ከተማ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ይገኛሉ። ዘርፉ ለስራ እድል ፈጠራ ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ ፕሮግራሙ ተኪና የኤክስፖርት ምርቶችን ከማምረት ባለፈ ለስራ እድል ፈጠራ አንዱና ትልቁ ትኩረት ሊሆን ይገባል፡፡ የገበያ ትስስር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት በመስራት የዘርፉን እድገት ይበልጥ መሳደግ ይጠበቃል፡፡

ግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ያለውን ሰፊና የእንስሳት ሀብት በማልማት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በዘርፉ ሰፊ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ የእንስሳት ዘርፉን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የስርዓተ ምግብ ሽግግር ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም በሀገር አቀፍ ደረጃ በመቅረጽ በተመረጡ የእንስሳት ሀብት ዘርፎች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ መርሃ ግብሩ በታሰበው መንገድ እየተከናወነ ሲሆን፣ በሰው ሰራሽ ማዳቀል፣ በዶሮ ጫጩት እና በዘመናዊ የንብ ቀፎ ስርጭት እንዲሁም በዓሳ ጫጩት ስርጭት ላይ በስፋት እየተሰራ ነው፡፡

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዶሮ፣ ወተት፣ በንብና ዓሳ ላይ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል። በተለይ ለከተማ ነዋሪዎች፣ ለአርሶና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የተለየ አጋጣሚን የፈጠረ ነው፡፡ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የምግብ ምርቶችን ለማምረት፣ ኤክስፖርትን ለማሳደግና ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር ትልቅ ድርሻ አለው፡፡

ዘርፉ የስነ ምግብ ዋስትናን ለማስፈን ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ሲሆን፣ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር አንዱ ማሳኪያ መንገድ ነው፡፡ በመርሃ ግብሩ ከ26 ሺህ በላይ የሌማት ትሩፋት መንደሮች መመስረታቸውንና በተፈጠሩ መንደሮች የግብዓትና ቴክኖሎጂ አቅርቦት ፍላጎቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡ በዚህ መነሻነትም አቅርቦትና ፍላጎቱን ለማመጣጠን ግብዓቶች የሚቀርቡበት መንገድ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

የ“ሌማት ትሩፋት” መርሐ-ግብር የእንስሳት ተዋእፆ የምርት እምርታን ማረጋገጥ እና ከእምርታው ፍሬም የመቋደስ ግብ ሰንቋል። ለእንስሳት የሚስማማ አየር፣ ለንቦች አመቺ የሆነ ስነ-ምህዳር፣ ስጋ እና እንቁላል ሊያትረፈርፍ የሚችል ተፈጥሮም ያላት አገር ናት ኢትዮጵያ። ይህንን አቅም ከመጠቀም አንጻር ግን አሁንም ብዙ ርቀቶች ይቀራሉ፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በአርባ ምንጭ ተገኝተው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት፣ የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የዜጎችን የምግብ መሶብ ከማሳ ጋር የሚያስተሳስር መሆኑን ማብራራታቸው የሚታወስ ነው፡፡

በይግለጡ ጓዴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review