የልማቱ ሌላኛው ትሩፋት

የ68 ዓመት የእድሜ ባለጸጋው አቶ መሀሪ እጅጉ ከአራት ኪሎ ፒያሳ በሚወስደው መንገድ ላይ በአካባቢው ልማት በመደመም ሲንቀሳቀሱ ነበር አግኝተን ያነጋገርናቸው፡፡ “ትውልዴና እድገቴ እዚሁ አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል ጀርባ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ እያየሁት ያለው አሁናዊ ለውጥ በእድሜየ አይቸው አላውቅም፡፡ የመንገዱ ስፋት፣ ምቾቱና ውበቱ ግርምትን ፈጥሮብኛል፡፡ መንገድ ዳር ላይ የተሰራው ደረጃውን የጠበቀ የህዝብ መጸዳጃ ቤት፣ አስፋልት ዳር ላይ ያለው የታክሲና አውቶቡስ ማውረጃና መጫኛ፣ ለእግረኛ ማረፊያ የተሰራው መናፈሻ እንዲሁም ሰፊ የመኪና ማቆሚያ ግርምትን የሚያጭር ነው” በማለት ነበር አስተያየታቸውን መስጠት የጀመሩት፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ከልጅነት እስከ እውቀት ድረስ በተለያዩ ጊዜያት ለውጦችን እያዩ መምጣታቸውን ጠቅሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም አሁን የተጀመረው የኮሪደር ልማት ልዩና አስደናቂ ስለመሆኑ አጫውተውናል፡፡ ቀደም ሲል በመተላለፊያ መንገዶች መጥበብ ምክንያት ሰውና መኪና እየተገፋፉ ነበር የሚጓዙት፡፡ ለተሽከርካሪዎች የተለየ ማቆሚያ በሚፈለገው ልክ  አልነበረም። በዚህ እና መሰል ምክንያቶች በእግረኞች ላይ አደጋዎች ይበዙ ነበር፡፡ የኮሪደር ልማቱ ይህን ችግር በመቅረፍ ረገድ ያለው አበርክቶ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡” ሲሉ ሀሳባቸውን አጋርተውናል፡፡

ከአራዳ ክፍለ ከተማ ፊት ለፊት የተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የመኪና ማቆሚያ

ለ20 ዓመታት ያህል በማሽከርከር ሙያ የተሰማሩት አቶ ሳሙኤል ታደሰ በበኩላቸው፣ በመዲናዋ በቂ የመኪና ማቆሚያ ባለመኖሩ ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጡ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ጉዳያቸውን ለመፈጸም መኪናቸውን መንገድ ላይ አቁመው ሲወርዱ የጎን መስታወት፣ የዝናብ መጥረጊያ ጎሚኖዎች… በሌቦች ይወሰዳሉ፡፡ ግብይት በሚፈጽሙባቸው አካባቢዎች ለምሳሌ መርካቶ አካባቢ የሚፈልጉትን ነገር ለመግዛት ያለመረጋጋት እና ጥራቱንና ዋጋውን ሳያዩና ሳያጣሩ በችኮላ ለመግዛት ይገደዱ እንደነበር ነው የሚናገሩት፡፡ ሌላው ችግር በመዲናዋ ያሉ መንገዶች ጠባብ እና በቂ ማቆሚያ የሌላቸው ከመሆናቸው የተነሳ ደርበው ለመቆም ይገደዳሉ፡፡ በዚህም ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ይፈጠራል፡፡ ከሚፈጥረው የትራፊክ መጨናነቅ ባለፈም ደርቦ በቆመው መኪና ተከልልለው ለመሻገር የሚፈልጉ እግረኞች የመገጨት አደጋ ሲያጋጥማቸው ይስተዋላል፡፡

አሁን በተለያዩ የመዲናዋ አካባቢዎች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ተጠናቅቆ ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎት ሲውል ቀደም ሲል በመዲናዋ ይከሰቱ የነበሩ ችግሮችን በብዙ ይቀርፋል፡፡ አንደኛ መንገዶቹ ምቹና የተለየ የመኪና ማቆሚያ፣ የታክሲ መጫኛና ማውረጃ እየተበጀላቸው በመሆኑ ለሌባ የመጋለጥ ችግርን ያስወግዳል፡፡ ሌላው ጠባብ የነበሩት መንገዶች እንዲሰፉ በመደረጉ አሽከርካሪዎች የመንገዳቸውን ጠርዝ ይዘው ቢቆሙም ለሌሎች ተሽከርካሪዎች እንቅፋት አይሆኑም። አሁን ላይ እየተሰሩ ያሉት መንገዶች በአንድ ጊዜ ሁለትና ሶስት ረድፍ ተሽከርካሪን ማሳለፍ የሚችሉ ናቸው፡፡ ይህም የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር በማድረግ ረገድ የላቀ ሚና ይጫወታል ሲሉ አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡

አቶ ፋሲል ግርማን ደግሞ በአራት ኪሎ ፒያሳ መንገድ ላይ በተሰራው የመኪና ማቆሚያ መኪናቸውን አቁመው ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ሲወጡ ነበር አግኝተን ያነጋገርናቸው፡፡ “የመኪና ማቆሚያው እፎይታ ሰጥቶኛል፡፡ ያለምንም ስጋትና ፍርሀት ለማቆም የሚያስችል ነው፡፡ ምቹ ከመሆኑም በላይ ቀደም ሲል ለፓርኪንግ ይከፍሉት የነበረውን ከፍተኛ ብር ያስቀራል፤ አቅምንም ያገናዘበ ነው፡፡ የትራፊክ ፍሰቱንም የተሻለ አድርጐታል” ብለዋል፡፡

ሌላው በዚሁ አራት ኪሎ ፒያሳ በሚገኘው የመኪና ማቆሚያ መኪናቸውን ሲያቆሙ አግኝተን ያነጋገርናቸው መልአከ ብርሃን መርሻ ይባላሉ፡፡ እሳቸውም በመዲናዋ ለተሽከርካሪ የተለየ ማቆሚያ በሚፈለገው ልክ ባለመኖሩ ያጋጥማቸው የነበረውን ችግር ገልጸውልናል፡፡ በገለጻቸውም፤ ምንም እንኳን መኪና ቢኖራቸውም ማቆሚያ ስፍራ ባለመኖሩ መኪናቸውን ይዘው አይወጡም ነበር፡፡ መኪና የሚይዙት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ሲሄዱ ብቻ ነበር፡፡ ብዙውን ጊዜ ወደ ከተማ ሲወጡ ይጠቀሙ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ራይድ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት መኪናቸውን ይዘው ሊወጡ የቻሉት እንዲህ ዓይነት የተለየ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ በመሰራቱ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ድጋፍና ክትትል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢዘዲን ሙስባህ በኮሪደር ልማቱ እየተሰሩ ስላሉ የፓርኪንግ አገልግሎት እና ስለሚኖራቸው ፋይዳ ለዝግጅት ክፍሉ አብራርተዋል፡፡ እንደ አቶ ኢዘዲን ማብራሪያ፤ ቀደም ሲል በመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎች በተለየ ራሱን ችሎ ባለመኖሩ የትራፊክ ፍሰቱ ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነበር፡፡ በተለይም የተሽከርካሪ መተላለፊያ መንገዶች ጠባብ ከመሆናቸውም ባለፈ ራሱን የቻለ የማቆሚያ ስፍራ ባለመኖሩና በዳርና በዳር ተሽከርካሪዎች ይቆሙ ስለነበር የትራፊክ ፍሰቱ ከመታወኩ ባለፈ በእግረኛና በተሽከርካሪ ላይ አደጋ ይደርስ ነበር፡፡ እንዲሁም ተሽከርካሪዎችን ላልተገባ ስርቆት ያጋልጥ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት በኮሪደር ልማቱ ከመንገድ መሠረተ ልማት ጋር በተያያዘ እየተሠራ ካለው ልማት አንዱ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ነው። እንደየቦታው ተጨባጭ ሁኔታ ዲዛይኖቹ እየተስተካከሉ እየተሰሩ ነው፡፡ ቤዝመንት ሁለትና ሦስት ድረስ ያላቸው የመኪና ማቆሚያዎች አሉ፡፡ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎቹ ተርሚናልም ያላቸው ናቸው፡፡ በአምስቱም ኮሪደሮች የመዲናዋል ደረጃ የሚመጥኑ እንዲሁም የከተማዋን እድገት ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ተገንብተዋል፤ በመገንባት ላይም ናቸው፡፡ ተገንብተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩትና በመገንባት ላይ የሚገኙት የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎችም፤ ከቦሌ በመገናኛ – አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ኮሪደር 2 ሺህ 686 ተሽከርካሪዎችን የመያዝ አቅም ያለው በ9 የተለያዩ አካባቢዎች፣  ከሜክሲኮ – ሳርቤት- ወሎ ሰፈር ኮሪደር 500 ተሽከርካሪዎችን የመያዝ አቅም ያለው ወሎ ሰፈር አካባቢ፣  ከአራት ኪሎ – እስጢፋኖስ – ቦሌ ድልድይ ኮሪደር 1 ሺህ 506 መኪናዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው በ7 የተለያዩ አካባቢዎች፣  ከአራት ኪሎ – መገናኛ ኮሪደር ቀበና 150 ተሽከርካሪዎችን የመያዝ አቅም ያለው በኪዳነ ምህረት ት/ቤት አጠገብ እና ቤለር ሜዳ ከፍ ብሎ እንዲሁም ከዓድዋ – 4 ኪሎና የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያና የወንዞች ዳርቻ ልማት ኮሪደር 1 ሺህ 809 መኪናዎችን ማስተናገድ የሚችል በ5 የተለያዩ ስፍራዎች ላይ የመኪና ማቆሚያዎች እየተሠሩ ነው። ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉት ከ4 ኪሎ – ራስ መኮነን ድልድይ፣ ከሜክሲኮ – ሳርቤት፣ ከደጎል- አብርሆት ቤተ መጽሀፍት – ማህሙድ – ቴዎድሮስ አደባባይ – ወዳጅነት አደባባይ  ናቸው፡፡

የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎቹ አብዛኞቹ ሁለትና ሦስት ቤዝመንት ያላቸው ሲሆኑ ከላይ ሲታዩ በልምላሜ ያጌጡና የተዋቡ፣ ሰዎችና ህፃናት ለመዝናኛነት የሚጠቀሙባቸው ኘላዛ ናቸው፡፡

በዘመናዊ መልክ የተሰሩና እየተሠሩ ያሉት እነዚህ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ከተማዋ ውብና ፅድ፣ ደረጃዋም ከፍ እንዲል አበርክቶቸው ትልቅ ነው፡፡ ተሽከርካሪም ሆነ እግረኛ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ ዕድል ይሰጣሉ፡፡ በትራፊክ ፍሰቱ ላይ የነበረውን የመጨናነቅ ችግር በብዙ ይቀርፋሉ፡፡ እግረኛ በእግረኛ ተሽከርካሪም በተሽከርካሪ ነፃ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ ይደርስ የነበረውን አደጋ እንዲቀንስ ያግዛሉ። ሌላው ተሽከርካሪዎች በእግረኛ መንገድ ላይ ሲያቆሙ ለስርቆት ይዳረጉ ስለነበር የመኪና ባለቤቶችን ካልተገባ ስርቆት ይታደጋሉ። በቀጣይም እንደአስፈላጊነቱ መጨናነቅ በሚታይባቸው በተለያዩ አካባቢዎች እየተለየና እየተጠና የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች ይገነባሉ ሲሉ አቶ ኢዘዲን ገልጸዋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ባለው የኮሪደር ልማት አንድ አካል የሆነው የመኪና ማቆሚያ ስፍራ በተለየ እየተሰራ መሆኑ የትራፊክ ፍሰቱን በማሳለጥ ረገድ ስለሚኖረው ፋይዳ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ዲባባን የዝግጅት ክፍሉ አነጋግሯቸዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ግቡ የከተማዋን የትራፊክ ፍሰትና ደህንነት ማረጋገጥ ነው፡፡ በመዲናዋ በተለይም በስራ መውጫና መግቢያ ሰዓት የትራፊክ መጨናነቅ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የባለስልጣኑን አላማ የሚያሳካ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ 48 ኪ.ሜ የተሽከርካሪ መንገድ ደረጃውን በጠበቀና በአዲስ መልክ እየለማ ሲሆን ይህም መጨናነቅ ባለባቸው መስመሮች የትራፊክ ፍሰቱን ሰላማዊና ምቹ ያደርገዋል። ካለው የተሽከርካሪ መጨመር ጋር ተያይዞ በነበረው ጠባብ አስፋልት ላይ የመጫኛና ማውረጃ ችግር መኖሩ ሰዎችን ለአደጋ ሲያጋልጥ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት አስፋልቱ ሰፍቶ እንዲሰራ ከመደረጉም በላይ የመኪና ማቆሚያዎች መሰራታቸው እንቅስቃሴውንና ፍሰቱን ምቹ በማድረግ ሰዎች ከአደጋ እንዲጠበቁ ያደርጋል፡፡ ለእግረኞችም ቢሆን አማራጭ የትራንስፖርት እድሎችን የሚያመጣ ነው፡፡ በዋናነት ሞተር አልባ ተሽከርካሪዎችን እንደ ብስክሌት የመሳሰሉትን እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው፡፡ ሌላው ሰዎች አጫጭር መንገዶችን በእግራቸው እንዲጓዙ ማድረግ ነው፡፡ አምስት ኪሎ ሜትር የመሮጫ ትራኮች እየተሰሩ መሆኑ ደግሞ ህብረተሰቡ ጤናማ አኗኗር እንዲኖር እድል የሚሰጥ መሆኑንም አክለዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review