AMN – የካቲት 4/2017 ዓ.ም
የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተሥፋዬ በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን አንስተዋል።
ባለፋት ስድስት ወራት የተከናወኑ ሥራዎችን ጠቅሰው በተለይም ገቢ የመሠብሠብ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢሆንም በሚመነጨው ኢኮኖሚ ልክ ገቢን ማጠናከር ግን በቀጣይም በትኩረት መታየት አለበት ብለዋል።
መማር እያለባቸው በሰላም እጦት ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውንም አንስተዋል።
የልጆች ከትምህርት ገበታ ማቋረጥ ወላጅ የኾነን ሁሉ ሊያሳስብ ይገባል ብለዋል።
በመኾኑም ሰላምን ፈጥኖ ማረጋገጥ እና ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት በሙሉ እንዲማሩ በልዩ ትኩረት መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ነፍጥ አንግበው የልጆችን የዕውቀት ገበታ የሚዘጉ አካላትን ሕዝቡ በጋራ ቆሞ “ተው” ማለት መቻል አለበት ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በክልል እና በፌዴራል መንግሥት እየተሠሩ ያሉ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ሕዝብን ተጠቃሚ እንዲያደርጉም በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የዘገዩትን ላይ ደግሞ አፋጣኝ የእርምት ርምጃ መወሰድ እንዳለበት አሳስበዋል።
ዋና አፈ ጉባኤዋ የምክር ቤቱን 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ አጀንዳዎችንም ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል።