የሕንድ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የቴክኖሎጂ መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ

You are currently viewing የሕንድ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የቴክኖሎጂ መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ

AMN- መስከረም 22/2017 ዓ.ም

የሕንድ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የቴክኖሎጂ መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው አስታወቁ።

በሕንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ብዙነሽ መሰረት ዋና ተቀማጭነቱን በሕንድ ካደረገው የዓለም የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ማህበር(WASME) ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደር ብዙነሽ በማህበሩ ስር ለሚገኙ የሕንድ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት እና የንግድ እድሎች ገለጻ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ በዲጂታል ትራንስፎሜሽን አጀንዳ አማካኝነት “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂን ተግባራዊ እያደረገች እንደምትገኝ አምባሳደሯ ገልጸዋል።

ስትራቴጂው የዲጂታል እድሎችን በመጠቀም ኢትዮጵያን ወደ ዘላቂ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ መንገድ መምራት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመት እና በማበረታቻ ማዕቀፎች ሰፋፊ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የዓለም የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ማህበር ከፍተኛ አማካሪ እና የልዑኩ መሪ ኢንጂነር ራሜሽ ኩማር የኢትዮጵያ እና ሕንድ የሁለትዮሽ ትብብር ማጠናከር የሚያስችሉ በርካታ አቅሞችን መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።

የሕንድ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በሳይበር ደህንነት፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በሶፍትዌር ማበልጸግ፣ በኤሌክትሮኒክስ አስተዳደር፣ በኢንተርኔት ኔትወርክ ስርዓት፣ የምናባዊ እውነታ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ተያያዥ መስኮች ላይ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው አመልክተዋል።

የዓለም የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ማህበር በኢትዮጵያ የንግድ እና ኢንቨስትመንት እድሎች ለመመልከት የንግድ ልዑኩን ወደ ኢትዮጵያ የመላክ እቅድ እንዳለው ተጠቁሟል ።

ማህበሩ እ.አ.አ በ1980 የተቋቋመ ሲሆን ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እድገት እና ልማት የሚሰራ ድርጅት መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review