AMN – ጥር 22/2017 ዓ.ም
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባው የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል፡፡
የረቂቁን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) አቅርበዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ትምህርትን በእኩልነት እና ፍትሃዊነት በመላ ሀገሪቷ ተደራሽ ለማድረግ የጎላ ሚና እንዳለው ሰብሳቢው አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም፣ ረቂቅ አዋጁ የመምህራንን ጥራት እና ጥቅም የሚያስጠብቅ፣ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እና የትምህርት አስተዳደሩን ብቃት ለማረጋገጥ ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን ነገሪ (ዶ/ር) ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም፣ የአስተማሪነት ሙያ እንዲከበር እና በሂደትም የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ለመስጠት ረቂቅ አዋጁ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ አዋጅ ቁጥር 1368/2017 ሆኖ በሁለት ተቃውሞ፣ በአሥር ድምጸ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ መጽደቁን የምክር ቤቱ መረጃ ያሳያል፡