AMN- ጥቅምት 20/2017 ዓ.ም
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ነገ መደበኛ ስብሰባውን ያደርጋል።
በመደበኛ ስብሰባው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ መስከረም 27 ቀን 2017 ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት በሚቀርቡ ጥያቄዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ።
ይህን ተከትሎም ምክር ቤቱ የመንግስትን አቋም በማዳመጥ የድጋፍ ሞሽኑን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በስብሰባው ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።