የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች የብቃት ማረጋገጫ ምዝገባና እውቅና ሥርዓት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

You are currently viewing የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች የብቃት ማረጋገጫ ምዝገባና እውቅና ሥርዓት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

AMN-መጋቢት 9/2017 ዓ.ም

የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች ያጋጠማቸውን ችግሮች በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

በምክክር መድረኩ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በነበረው የትምህርት ሥርዓት ችግር መሠረታዊ የሞራል ውድቀት አጋጥሟል ብለዋል፡፡

ይህንንም ለማስተካከል በትምህርት ዘርፉ በአጠቃላይ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት የተለያዩ ሪፎርሞች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።

እነዚህ የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ መምህራን ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን፣ ለዚህም የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች ጥራት እና ብቃት ያላቸው መምህራንን በማፍራት ረገድ ተልኳቸውን እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች ድርሻ የላቀ መሆኑን አንስተዋል።

በመምህራን ስልጠና ረገድ ሀገራችን ረዘም ያለ ታሪክ ያላት መሆኗን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ አሁን ባለው ሁኔታ በሚያስተምሩበት የትምህርት ደረጃ በቂ ችሎታ ያላቸው መምህራንን በማፍራት ረገድ ተግዳሮቶች ገጥመዋል ብለዋል።

በዚህም ከመምህራን ስልጠና እና አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮችን በሚገባ ለይቶ መፍታት ካልተቻለ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ እንደማይቻል ጠቅሰው ይህንን ለመፍታት ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የጥራት ኦዲት መሪ ሥራ አስፈፃማ ወ/ሮ ትዕግስት ኃይለ ሥላሴ በበኩላቸው የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች ሥራቸውን በሚገባ እንዲሰሩ ወደ ብቃት ማረጋገጫ ምዝገባና እውቅና ሥርዓት እንዲገቡ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

በቀጣይ ኮሌጆቹ ምዝገባ በማድረግ የብቃት ማረጋገጫ እውቅና ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱበት ሥርዓት ተግባራዊ እንደሚደረግ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review