AMN – ታኅሣሥ 26/2017 ዓ.ም
የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቱ መጠን ከፍ እያለ እየመጣ በመሆኑ ጉዳት እንዳይከሰት ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ ስፔስ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አታላይ አየለ (ፕ/ር) አሳሰቡ።
ትላንት ሌሊት 9:52 ሰዓት ላይ በአቦምሳ የተከሰተው በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 8 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ሰሞኑን በአፋር ክልል አካባቢዎች ሲከሰቱ ከነበሩ ከፍተኛው መሆኑን ተናግረዋል።
በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት በአዲስ አበባ የተሰማው የመሬት ንዝረትም በመጠኑ ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር አታላይ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል አንደገለጹት የመሬት ንዝረቱ በሕንፃዎችም ሆነ በሌሎች ቤቶች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ይሰማ ነበር።
ነገር ግን እስካሁን በንዝረቱ ምክንያት በአዲስ አበባ የተፈጠረውን ጉዳት ለማወቅ እንደማይቻል ተናግረዋል።
የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቱ መጠን ከፍ እያለ እየመጣ በመሆኑ ጉዳት እንዳይከሰት ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
መደረግ ካለባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች መካከልም፥ ቁምሳጥን ላይ የሚቀመጡ ውድ እና ተሰባሪ እንዲሁም ተቀጣጣይ የሆኑ ዕቃዎችን መሬት ላይ ማስቀመጥ፣ የመሬት ንዝረቱ ቅፅበት እስከሚያልፍ ማዕዘን አካባቢ መቆም እና ጠረጴዛ ስር እና ጭንቅላትን መከላከል በሚያስችሉ ቦታዎች መከለል እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ-ኃይሎችም ችግር ቢደርስ በአስቸኳይ ለመፍታት ከወዲሁ ሰፊ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
በአቦምሳ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ጠንካራ እና ብዙዎችን ከእንቅልፋቸው የቀሰቀሰ ሲሆን በርካቶችም ክስተቱን በተለያዩ የማኅበራዊ ትሥሥር ገጾች ሲገልጹ ነበር።
በዮናስ በድሉ