AMN-ጥቅምት 19/2017 ዓ.ም
የመሬት አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ ብልሹ አሰራሮችን መቆጣጠር መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ገለፀ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመሬት እና ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሪፎርም ዙሪያ ውይይት እያካሄዱ ነው።
ቢሮው የማህደርና ስፓሻል መረጃ አያያዝ ማሻሻሉን እና ገቢ እና ወጪ ደብዳቤዎች በሲስተም በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ማድረጉን ገልጿል።
ባለጉዳይ አገልግሎት ለማግኘት ሲመጣ በአሻራ ብቻ የሚሰጥ በመሆኑ ከብልሹ አሰራር ነጻ ለማድረግ ተችሏል ተብሏል ።
የቢሮው ሪፎርም በቴክኖሎጂ መሰረት ልማት ግንባታ እና ተቋማት ኔትወርኪንግ ፣ በመሬት አገልግሎት ሲስተም ልማት ፣ በመረጃ ዲጂታይዜሽንና አስተዳደር ስርዓት ፣ በተቋም አደረጃጀት እና ህጎች ማሻሻል ፣ በቅንጅታዊ አሰራር እና በምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር ላይ ስኬታማ ስራዎች መስራት መቻሉንም ገልጿል።
የመሬት ይዞታ አገልግሎት ከ100 አመት በላይ ያስቆጠረ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የተገኙ ውጤቶች የኦንላይን አገልግሎት፣ ብልሹ አሰራሮችን መቆጣጠር እና የመረጃ ተዓማኒነት ማረጋገጥ መቻሉም ተመላክቷል።
የአዲስ አበበ ከተማ ምክር ቤት የመሬት እና ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ኒዕመተላህ ከበደ፣ ቢሮው አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረጉ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡ይህም የአዲስ አበባን የረዥም ጊዜ የመሬት አያያዝ ችግር የፈታ ነውም ብለዋል፡፡
ጉዳዩን በአግባቡ የሚረዳ የሰው ሐይል ማፍራት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።
በዳንኤል መላኩ