AMN – መስከረም 14/2017 ዓ.ም
የመስቀል ደመራና ኢሬቻ በዓላት ሐይማኖታዊ እና ባህላዊ ስርዓታቸው ተጠብቆ እንዲከበሩ ሴቶች የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ጥሪ አቀረበ።
ቢሮው በመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት አከባበር ዙሪያ ከአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር ከተማ አቀፍ የሴቶች ውይይት እያካሄደ ነው።
የቢሮው ሃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ፣ የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላትን በድምቀት ለማክበር በርካታ ህዝብ አደባባይ የሚወጣ በመሆኑ በአላቱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትዉፊታቸዉን ጠብቀው በድምቀት ይከበሩ ዘንድ የከተማዋ ሴቶች ሚናቸዉ የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተለይም የዓለም ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ የተመዘገበው የመስቀል ደመራ በዓል እና የፍቅርና የአንድነት መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል እንደሁልጊዜው ሁሉ ዘንድሮም በተሻለ ድምቀት እንዲከበሩ ሴቶች የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
በዓላቱ አሁን ያለውን ሰላም በማጽናት አንድነትን እና ሕብረትን የምናሳይበት መሆን አለበት ሲሉ ገልፀዋል።
“ሴቶች ለሰላም ሰላም ለሴቶች” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ በሚገኘው ውይይት ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሴቶች እየተሳተፉ ነው።
በሄለን ጀንበሬ