AMN – መስከረም 14/2017 ዓ.ም
የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ እና አንድነትን በሚያጎላ መልኩ እንዲከበር የኃይማኖት አባቶች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የመስቀል ደመራ በዓል አከባበርን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶችን ያሳተፈ የማጠቃለያ ውይይት አካሂዷል።
በዚህ የማጠቃለያ ውይይት ላይ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁህ አቡነ ሄኖክ፣ የገዳምና የአድባራት ሀላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ፀሀፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ተገኝተዋል።
ቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ የመስቀል ደመራ በዓል በከተማዋ በሚገኙ 251 አድባራት እና በመስቀል አደባባይ በተገቢው ኃይማኖታዊ ስነ ስርዓት እንዲከበር የእምነቱ አባቶች ድርሻ ትልቅ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ከአገር የማይዳሰሱ ቅርሶች የሚመደበው መስቀል ደመራ የቤተክርስቲያኗ ብቻም ሳይሆን የአገር ቅርስ ነው ያሉት ወይዘሮ ሊዲያ በዓሉ ያለ ምንም የፀጥታ ስጋት እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በውይይቱ የተገኙ የቤተክርስቲያኗ አባቶች የደመራ ስነ ስርዓት በጊዜና ስርዓቱን ጠብቆ እንዲከናወን ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በተለይም በመስቀል አደባባይ በሚኖረው ስነ ስርዓት ተገቢውን መንፈሳዊ አገልግሎቶች ለማስተላለፍ እንዲቻል የሰዓት አጠቃቀም ላይ ትኩረት እንዲደረግም ጠይቀዋል።
በማጠቃለያው ይህ በዓል አንድነትን በሚያሳይ መልኩ እንዲከበር የሰላም ማስጠበቅ ስራው ቅድሚያ እንደተሰጠው የተነገረ ሲሆን ይህም የኢትዮጵያን ገፅታ ለማስተዋወቅ ይረዳል ተብሏል።
በትዕግስት መንግስቱ