የመስቀል ደመራ በዓል በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ንግሥት እሌኒ ግማደ መስቀሉን ከማግኘቷ ጋር በማያያዝ የሚከበር በዓል ነው።
መስከረም 16 እና 17 ቀን የሚከበረው የደመራ እና መስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ አስተምህሮውም ባለፈ ባህላዊ ትውፊትነቱ የጎላ በመሆኑ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ይናፈቃል።
ደመራ እና መስቀል የአንድነት፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ አብሮነት፣ የምስጋና እና የተስፋ እሴቶች የሚገለጹበት ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው።
የኢትዮጵያ የመስቀል በዓል አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የትምህርት እና ባህል ተቋም (ዩኒስኮ) መዝገብ ውስጥ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለመስቀል ችቦ እያበሩ በዓሉን በሆታ በእልልታ በስብሐተ እግዚአብሔር ያከብሩታል።
የመስቀል በዓል በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በልዩ ድምቀት ከሚከበሩት በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን እንደየአከባቢዎቹ ባህል እና ትውፊት መሠረትም በተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ሁነቶችም ይከበራል፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ እንደ ዘመን መለወጫ ይቆጠራል።
መስቀል በጉራጌ
በጉራጌ ዘንድ መስቀል ከሁሉም በዓላት የበለጠ በናፍቆት የሚጠበቅ ሲሆን እንደ አውራ በዓልም ይቆጠራል። በዓሉ የተራራቁ ቤተሰቦች የሚገናኙበት የፍቅር፣ የደስታ እና የእርቅ በዓል ነው። ለበዓሉም ዓመቱን ሙሉ ዝግጅት ይደረጋል። አባወራው ሰንጋ ለመግዛት፣ እማወራ ማጣፈጫውን ለማዘጋጀት፣ ወጣቶች ደመራ እና ደቦት ለማዘጋጀት፣ ልጆች ምርቃት ለመቀበል የየራሳቸውን ይዘጋጃሉ።
መስቀል በጎፋ
በጎፋ ዞን በጎፋ እና ኦይዳ ብሔረሰቦች ከሚከበሩ አያሌ ባሕላዊ በዓላት መካከል የመስቀል በዓል ቅድሚያውን ይይዛል።
የበዓሉ ሲያሜ በጎፋ ብሔረሰብ “ጋዜ ማስቃላ” ሲባል በኦይዳ ብሔረሰብ ደግሞ “ዮኦ ማስቃላ” በመባል ይጠራል፤ በዓሉ በክዋኔ ደረጃ በሁለቱ ብሔረሰቦች በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው።
ወርሃ መስከረም ሲገባ በጎፋ ብሔረሰብ የዓመት መለወጫ በዓል የሚከበርበት ወቅት ሲሆን በዚህም የአዲስ ዓመት ማበሰሪያ ምልክቶች ብቅ ብቅ ማለት ይጀምራሉ።
አካባቢው በብሔረሰቡ አጠራር ቤላ ጭሻ (Bella ciisha) ወይም በአደይ አበባ ጋራው ሸንተራሩ አቆጥቅጦ ሲያሽበርቅ በብሔረሰቡ ዘንድ በስፋት ከሚታወቀው ምርት በዋናነት ጤፍን በጊዜው ከአረም ነፃ የሚያደርጉበት ሰብሉ አብቦ የሚደምቅበት ወቅት መሆኑ ነው።
የመስቀል በዓል በሁለቱ ብሔረሰቦች ዘንድ እንደ ዘመን መለወጫም ተደርጎ ይወሰዳል መስቀል በጎፋ ትልቅ ትርጉም አለው።
ዮ…ማስቃላ በጋሞ
በጋሞዎች ዘንድ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቀው “ዮ ማስቃላ” የዘመን መለወጫ በዓል በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ቅበላው አከባበሩ ይጀምራል።
መስከረም ወር የመጀመሪያው ቀን በጋሞ ዞን ”ሂንግጫ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ይህም አዲሱን ዓመት ለመቀበል ዝግጅት የሚደረግበት ቀን ነው።
በጋሞዎች ዘንድ ዓመቱን ሙሉ ገንዘብ በመቆጠብ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ይደረጋል። ወንዶች ለበዓሉ የሚሆን ሠንጋ መግዣ፣ ለልጆች ልብስ እና ጌጣጌጥ ማሟያ፤ እናቶች ደግሞ ለቅቤ፣ ለቅመማቅመም፣ ለባህላዊ ምግቦች እና መጠጦች እህል መግዣ የሚሆን ገንዘብ ያጠራቅማሉ።
በጋሞ ዞን የማስቃላ በዓል ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለእንሳስት እና ለአዕዋፋትም ጭምር ነው ተብሎ ይታመናል፤ በዕለቱ ምግብ ከሰው አልፎ ለእንሳስት እና ለአዕዋፍም ይትረፈረፋል። ለከብቶችም የግጦሸ መሬት በየአካባቢው ይከለላል።
በተለያዩ አጋጣሚዎች የተጣሉ ታርቀው፣ የተራራቁ ዘመድ አዝማድ እና ወዳጆች ተሰባስበው በዓሉን በጋራ እንዲያከብሩ ማድረግ የጋሞ ማስቃላ በዓል መገለጫ ነው።
ያሆዴ መስቀላ በሃድያ
የክረምቱ ወራት አልፈው መስኩ በልምላሜ እና በአደይ አበባ ሲያሸበርቅ በሃድያዎች ዘንድ ትልቅ ዝግጅት አለ – ያሆዴ መስቀላ።
“ያሆዴ“ ማለት እንደ ብሔሩ የባህል ሽማግሌዎች ትርጓሜ እንኳን ደስ አላችሁ፤ የሚል የብስራት ትርጉም ያለው ሲሆን ”መስቀላ” ማለት ደግሞ ብርሃን ፈነጠቀ ማለት ነው። በመሆኑም ያሆዴ መስቃላ ብርሃን ፈነጠቀ እንኳን ደስ አላችሁ የሚል ትርጉም አለው።
በዓሉ በወርኃ መስከረም 16 የሚከበር ሲሆን ወሩ ብርሃን፣ ብሩህ ተስፋ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ረድኤት፣ በረከት የሚሞላበት ተምሳሌት ወር ተደርጎ ይቆጠራል።
የሃድያ አባቶች “ከባለቤቱ የከረመች ነፍስ በያሆዴ መስቀላ ትነግሳለች“ የሚል ብሂል አላቸው። የሃድያ አባቶች እንደ ዘመን መለወጫ የመጀመሪያ ቀን አድርገው በመውሰድ ማንኛውንም ዓይነት ክስተት ከዚያ ጋር አያይዘው እንደሚቆጥሩ ይነገራል።
መሳላ በጠንባሮ እና ዶንጋ ብሔረሰቦች
መሳላ በከንባታ፣ ጠንባሮና ዶንጋ ብሔረሰቦች ዘንድ በየዓመቱ የሚከበር በዓል ነው። በዓሉ በከምባታ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ታላቅ የዘመን መለወጫ በዓል ሲሆን የአሮጌው ዓመት ማብቅያ እና የአዲሱ ዓመት መጀመሪያ የመሸጋገሪያ በዓል ነው።
መሳላ ማለት (ታላቅ)፣ መጀመሪያ እንደ ማለት ሲሆን በዓሉ ከአሮጌ ወደ አዲስ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገር የሚለውን ይገልጻል።
ከምባታዎች አስራ አንድ ወራት በስራ ካሳለፉ በኋላ የመጨረሻውን አንድ ወር ለበዓሉ ያውሉታል።
የመጀመሪያዎቹን 15 ቀናት በበዓሉ ዝግጅት፣ ቀሪዎቹን ቀናት ደግሞ በሀሴት፣ በመዝናናት፣ በመጫወት በጋራ ያሳልፋሉ።
በአጠቃላይ የመስቀል በዓል በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ርዕሰ ዓውደ-ዓመት ይመስላል፤ በደቡብ ኢትዮጵያ መስቀል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባህላዊ ጎኑ ይጎላል።
በዓሉ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በሚመሳሰል ስም እና የአከባበር ሁኔታ የሚከናወን፣ የኅብረ-ብሔራዊነታችን መገለጫ ነው።
የኢትዮጵያውን አንድነት ከፍ ብሎ ከሚገለጽባቸው አጋጣሚዎች የመስቀል በዓል አንዱ ነው።
በዮናስ በድሉ