AMN – ታኅሣሥ 20/2017 ዓ.ም
በአማራ ክልል ታጥቀው ወደ ጫካ የገቡ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ ሕዝብና መንግሥት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ይህንን ጥሪ ጥሪ የተቀበሉ በርካታ ታጣቂዎችም የሕዝብንና የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ሲገቡ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
“እየሄድንበት ያለው መንገድ የሕዝባችንን ስቃይ የሚያባብስ በመሆኑ የሰላምን አማራጭ አስቀድመናል” ሲሉ ሕዝብና መንግሥት ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉና አቀባበል የተደረገላቸው የታጠቁ አካላት ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ከሰሜን ወሎ፣ ከደቡብ ወሎ ፣ ከሰሜን ሸዋ ፣ ከዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር፤ ከደሴ፤ ኮምቦልቻና ወልድያ ከተሞች እንዲሁም ከኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የታጠቁ አካላት የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ነው በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ምሥራቅ ዕዝ አባላት ነው አቀባበል የተደረገላቸው።
ታጣቂዎቹ የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች ለማስመለስ በሚል ወደ ጫካ መግባታቸውን ጠቅሰው፤ የተከተሉት መንገድ ግን የተሳሳተ እንደነበር አመላክተዋል።
በትጥቅ ትግሉ ምክንያት የመጀመሪያው ተጎጂ የክልሉ ሕዝብ ነው ያሉት ታጣቂዎቹ የሰው ህይዎት መጥፋት፣ የመንገድ መዘጋት፣ የጤና ተቋማት በተሟላ ሁኔታ ሥራ አለመጀመር፣ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አለመሄድና ተያያዥ ችግሮች መፈጠራቸውን ነው የገለጹት።
የሕዝብ ጥያቄ በዚህ ሁኔታ አይመለስም ያሉት የታጠቁት አካላት ችግሮችን ከመንግሥት ጎን በመሆን በውይይት መፍታት የተሻለ አማራጭ በመሆኑ በሕዝብና በመንግሥት የቀረበውን የሰላም ጥሪ በደስታ መቀበላቸውን ነው የተናገሩት።
በተሳሳተ መንገድ እስከዛሬ የበደልነውን ማኅበረሰብ ለመካስ ተዘጋጅተናል ያሉ ሲሆን ፣የሃገር የመጨረሻ ምሽግ ከሆነው ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ ለሰላም እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
እስካሁን ላደረሱት በደልና ለፈጸሙት ጥቃትም ህዝብና መንግስትን ይቅርታ ጠይቀዋል።
እንዲህ አይነቱ ጽንፍ ረገጥ የተሳሳተ አካሄድ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ ስለማይመለስ ጫካ ያሉ የታጠቁ አካላትም የሕዝብንና የመንግሥትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላደረገላቸው መልካም አቀባበልም አመስግነዋል።
በአቀባበሉ ላይ የተገኙ የኃይማኖት አባቶችም የሰላምን አስፈላጊነት በማንሳት ጥሪ ሲያስተላልፉ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ ይህንኑ ምርጫቸው አድርገው ለሰላም ቅድሚያ ለሰጡ የታጠቁ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
ለታጣቂዎቹ አቀባበል ያደረጉላቸው በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል አዛዥ ኮሎኔል ግርማ ስዩም በበኩላቸው መንግሥትና ሕዝብ ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የመጡ በርካታ የታጠቁ አካላት መኖራቸውን ገልጸዋል።
ሠራዊቱም የሰላም አማራጭን ላስቀደሙ ታጣቂዎች መልካም አቀባበል እያደረገላቸው መሆኑን አመላክተዋል።
በጫካ የሚገኙ ሌሎች ታጣቂዎችም የሰላምን መንገድ መርጠው ለሕዝብ እፎይታ እንዲሠሩ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘገባ ያመለክታል።