AMN – ጥር- 24/2017 ዓ.ም
የመንግስት የልማት ድርጅቶችን የተሟላና ዘመናዊ አገልግሎትን ከመስጠት ባለፈ ይበልጥ አትራፊ እና ተወዳዳሪ እንደሆኑ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ የመንግስት ልማት ድርጅቶች አስተዳደር ባለስልጣን ገለጸ።
ባለስልጣኑ በስሩ የሚገኙ 7 የመንግስት የልማት ድርጅቶችን የ2017 የ6 ወር የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ግምገማና ውይይት አካሄዷል።
የመንግስት ልማት ድርጅቶችን ይበልጥ ውጤታማ ፣ አትራፊ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ የመንግስት ልማት ድርጅቶች አስተዳደር ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባወይ ዮሐንስ ተናግረዋል።
ባለፉት 6 ወራት እና ከዛ ቀደም በተደረገው ጠንካራ ድጋፍና ክትትል ኪሳራ ውስጥ የነበሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ከኪሳራ በማውጣት ትርፋማ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏልም ብለዋል አቶ አባወይ።
የኤግዚቢሽን ማዕከልና ገበያ ልማት ድርጅት ፣ የአዲስ አበባ የኮንስትራክሽን ዲዛይን ፣ ግንባታና ማማከር ድርጅት ፣ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ፣ ከነማ ፋርማሲዎች ድርጅት ፣ የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ፣ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር አስተዳደር እና የንግድ ስራዎች ድርጅትን የልማት ድርጅቶችን የተቋማቸውን የአፈጻጸም ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተካሄዷል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 84/2016 አንቀጽ 40 የተቋቋመ ሲሆን የመንግስት የልማት ድርጅቶችን የመከታተል የመቆጣጠር እና የመደገፍ ኃላፊነት ያለበት ተቋም መሆኑም ተጠቁሟል።
በዳንኤል መላኩ