AMN – መጋቢት 2/2017 ዓ.ም
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የመካከለኛው ዘመን የገቢ አሰባሰብ ስትራቴጂ የሀገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገለጹ፡፡
“የልማት ግቦችን ለመደገፍ የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን ማጎልበት “ በሚል መሪ ሀሳብ፣ 11 የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተሳተፉበት የሀገር ውስጥ ገቢ ማሳደግን ዓላማ ያደረገ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ፣ ኢትዮጵያ በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሀገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግ በትኩረት እየሠራች ትገኛለች ብለዋል።

የዚህ አካል የሆነው ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገች የምትገኘው የመካከለኛው ዘመን የገቢ አሰባሰብ ስትራቴጂም የሀገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው፣ በጉባኤው ኢትዮጵያ በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው በገቢ ዘርፍ ያከናወነችውን ተሞክሮ ታካፍላለች ብለዋል።
የሀገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግም ገቢዎች ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የገቢዎች ሚኒስቴር ከአይ ኤም ኤፍ ጋር በጋራ ያዘጋጀው ይህ መድረክ ዛሬን ጨምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።