ባለፉት ቀናት በመዲናችን የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ኩነቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል ዝግጅቶች የተሰናዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል የስዕል አውደ ርዕይ፣ አዳዲስ የመጽሐፍ ህትመት፣ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ የቴአትር መርሃ ግብር፣ ኪነ ጥበባዊ ውይይቶች ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል የተወሰኑትን መርሃ ግብሮች እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

መጽሐፍት
በገጣሚ ብሩክ በቀለ ንጉሴ የተጻፈው “ሻሞ” የተሰኘ የግጥም መድብል ባሳለፍነው ሳምንት ለንባብ የበቃ ሲሆን፣ በተለያዩ የመጽሐፍት መሸጫ መደብሮች ላይ ይገኛል፡፡
በሌላ መረጃ በኤፍ ኤም 97.1 ሬድዮ ላይ የተላለፉ የእንዶድ የሬድዮ ፕሮግራሞች በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ለአንባቢያን ሊደርስ ነው፡፡ የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ መኮንን ሞገሴ በማህበራዊ የትስስር ገጹ ላይ ባጋራው መረጃ፣ “ከእኛው እኛው እንዶድ” በሚል ርዕስ በቅርቡ በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ለተደራስያን ይቀርባል ብሏል። ጋዜጠኛው ስለ ፕሮግራሞቹ እንዲህ ብሏል፤ “በአስተውሎት ንጽሕና፣ በአብሮነት መድህን፣ ከተፈጥሮ በተቀዳ ጽናት፣ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ሆኖ መገኘት መቻል እና ሌሎችን ማስቻልን መነሻው አድርጎ የሚሰናዳ የራዲዮ መሰናዶ ነው!”
የኪነ ጥበብ ምሽት
ታዋቂው ገጣሚና ደራሲ ፍሬዘር አድማሱን ጨምሮ ሌሎች ከያኒያን የሚሳተፉበት የጥበብ ምሽት ሊደረግ ነው፡፡ የፊታችን አርብ ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በአለያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ በሚደረገው በዚህ የጥበብ ምሽት ግጥም፣ የአንድ ሰው ተውኔትና የመድረክ ትወና እንዲሁም በዲጄ ሙዚቃ የታጀበ ግጥም ይቀርባል ተብሏል፡፡

ሥዕል
የሠዓሊ አለባቸው ካሣ ‘የተቀደሱ ማሚቶዎች’ የሥዕል አውደ-ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት አርብ ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም በሐያት ሪጀንሲረ ሆቴል ውስጥ በሚገኘው ፈንድቃ የባህል ማዕከል ውስጥ በይፋ የተከፈተው ይኸው አውደ ርዕይ፣ ሠዓሊ አለባቸው በተለያዩ ጊዜያት የሳላቸው የሥዕል ስራዎች የቀረቡበት ነው ተብሏል። የሥዕል አወደ ርዕዩ እስከ ፊታችን ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ለዕይታ ክፍት ሆኖ ይቆያል ተብሏል።
ሙዚቃ
ልዑል ሲሳይ ተከታታይ ኮንሰርት ሊያቀርብ ነው፡፡ የድምፃዊ ልዑል ሲሳይ ኮንሰርት የፊታችን ሚያዚያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት 6:00 ሰዓት ድረስ በጊዮን ሆቴል ይካሄዳል። ይህ ኮንሰርት እንደተጠናቀቀ ግንቦት 2 በሀዋሳ፣ ግንቦት 23 በድሬዳዋ ሌሎች ድምፃውያንን በማካተት የኮንሰርት ቱር እንደሚካሄድ ተገልጿል። ከልዑል ሲሳይ በተጨማሪ ስካት ናቲ፣ ሃና ግርማ እና ዊሃ በዝግጅቱ ላይ በቶራ ባንድ ታጅበው ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል።
የቴአትር መርሃ ግብር
በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ ከሚታዩ ቴአትሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል። ቅዳሜ 8:00 ሰዓት ባሎች እና ሚስቶች፣ 11፡30 ሰዓት ባቡሩ የተሰኙ ቴአትሮች በብሔራዊ ቴአትር ይታያሉ። እሁድ በ8፡00 ሰዓት 12ቱ እንግዶች፤ 11፡30 ሰዓት ላይ እምዬ ብረቷ በብሔራዊ ቴአትር ይታያሉ፡፡ ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሶስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ፣ ሐሙስ ቀን 11:30 ሰዓት ሸምጋይ፣ አርብ 11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይታያሉ፣ ጥቁር እንግዳ ተውኔት ሀሙስ በ12፡00 ሰዓት በዓለም ሲኒማ ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባል፡፡
በአብርሃም ገብሬ