የመዲናዋ ኪነ-ጥበባዊ መሰናዶዎች

You are currently viewing የመዲናዋ ኪነ-ጥበባዊ መሰናዶዎች

ባለፉት ቀናት በመዲናችን አዲስ አበባ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አዳዲስ የመጽሐፍት ምርቃትና ህትመት፣ የሥዕል ዓውደ ርዕይ፣ የሙዚቃ ስራዎች እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ይካሄዳሉ፡፡ ከእነዚህ ዝግጅቶች መካከል የመጽሐፍት ውይይት፣ የቴአትር መርሃ ግብር፣ የስዕል አውደ ርዕይ እና ሌሎች መሰናዶዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መርሃ ግብሮቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

መጽሐፍት

“ከራሚ ከራማ” የግጥም መድብል ለንባብ በቅቷል፡፡ በገጣሚ ዳንኤል ወዳጄ የተዘጋጀው፤ 96 ግጥሞችን እና  242 ገፆችን የያዘው  ይህ መድብል  በውስጡ  በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ስንኞችን አካትቷል። ገጣሚው እንደሚለው “ከራሚ” የሚለው ቃል ግዕዝም አማርኛም አንድምታ አለው። ግዕዙ “ወይን ጠጅ ጠማቂ” ማለት ሲሆን፣ አማርኛው ደግሞ “አልፋን ኦሜጋንም ያጠቃለለ ነው” የሚል ነው። በመግቢያው በደንብ እንደተጠቀሰውም የገጣሚው ምኞት በሥራው ኦሜጋ መሆን ነው። በተለያዩ ግጥሞቹም ይህ ምኞት ተንፀባርቋል።

በሌላ የመጽሐፍት መረጃ “የፒያሳ ቆሌዎች” የተሰኘው መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ መጽሐፉ በጃፓናዊ አንትሮፖሎጂስት የፊልም ባለሙያና ገጣሚ ኢትሱሺ ካዋሴ (ዶ/ር) የተጻፈ ሲሆን  በዓለማየሁ ታዬ እና በያዕቆብ ብርሃኑ ወደ አማርኛ ተተርጉሟል፡፡ ደራሲው በአሁኑ ወቅት በጃፓን ብሔራዊ የኤትኖሎጂ ሙዚየም በፕሮፌሰርነት ማዕረግ በማስተማር ላይ ይገኛል። መጽሐፉ የኢትዮጵያን ቱባ ባህል፣ ማንነት፣ ወግ፣ ጥበብና አኗኗር የሚዳስስ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ካዋሴ በኢትዮጵያ ለበርካታ ጊዜያት በመኖርና በመመላለስ ያካበተውን ልምድ መሰረት አድርጎ በጃፓን ቋንቋ የጻፈው መፅሐፍ ሲሆን  ‘Mischief of the Gods’ በሚል ርዕስ በጄፍሪ ጆንሰን ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሟል፡፡

ሥዕል

ሰባት ወጣት ሰዓሊያን በጋራ ያዘጋጁት የስዕል ዓውደ-ርዕይ ዛሬ መታየት ይጀምራል፡፡ “ሪትም” በተሰኘው በዚህ የሥዕል አውደ-ርዕይ ላይ ከተሳተፉት ወጣት ሰዓሊያን መካከል አለምሰገድ በሃይሉ፣ አሌክሳንደር ፍስሃዬ፣ ዳዊት ጎሳዬ፣ ማህሌት አፈወርቅ፣ ሳሙኤል እንዳለማው ይገኙበታል፡፡  መልከ-ብዙ ግለሰባዊና ማህበረሰባዊ ጭብጦችን የሚዳስሱ ስራዎች ይቀርቡበታል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ አውደ-ርዕይ፣ ዛሬ 8፡00 ሰዓት በላፍቶ ዘመናዊ የሥነ ጥበብ ጋለሪ በይፋ ይከፈታል፤ ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታትም ለተመልካቾች ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

በሌላ መረጃ፣ በኢትዮጵያ ዕይታዊ ጥበባት ወዳጆች ማህበር የተሰናዳ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዝግጅት ዛሬ ይካሄዳል። ከመርሐ ግብሮቹ አንዱ የሠዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን (ፕ/ር) የሥነ ጥበብ ስራ የሆነው “የሚያጤሰው ጠረጴዛ” ላይ ትኩረቱን ያደረገ ምክክር ማድረግ ነው፡፡

ከዚህ የውይይት መርሃ-ግብር በተጨማሪ በዚህ መሰናዶ በሠዓሊ እና የአለ የሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት መስራች አለ ፈለገሰላም ህሩይ አንድ መቶኛ ዓመት የልደት በዓል እንደሚታሰብ ኢቨንት አዲስ ሚዲያ ዘግቧል፡፡ ይህ መርሃ ግብር ዛሬ ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት ጀምሮ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚደረግ ይሆናል፡፡

በሌላ የሥነ ጥበብ መረጃ፣ የወጣት ሴት ሰዓሊያን የስዕል አውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ “Questioned & assured Existence” በሚል ርዕስ ሰዓሊ ትማር ተገኔ እና ሰዓሊ ፈትለወርቅ ታደሰ የፈጠራ ጥበብ ስራዎቻቸው ያቀረቡበት አውደ ርዕይ የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም በገብረክርስቶስ ደስታ ሙዚየም በይፋ ተከፍቷል። ዓውደ-ርዕዩ እስከ መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ሲሆን የጥበብ አፍቃሪያን የሰዓሊያኑን ስራዎች መጥተው እንዲጎበኙ ተጋብዘዋል፡፡

ፊልም

“አባ መልካ” የተሰኘ ፊልም ለዕይታ በቅቷል፡፡ በአፋን ኦሮሞ የተዘጋጀው “አባ መልካ” የተሰኘ ይህ ፊልም በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ በያዝነው ሳምንት  ነው ለዕይታ የበቃው፡፡ ፊልሙ የተመረቀው ታዋቂ አርቲስቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የፊልም አፍቃሪዎች በተገኙበት ነው።

“አባ መልካ” ፊልም በአባለታ የትወና ማዕከል ሰልጣኞች ተሳትፎ የተሰራ ነው። ፊልሙ በኦሮሞ ፊልም ኢንዱስትሪ እና የፊልም እድገት ውስጥ ትልቅ ሚና አለው። የፊልሙ ይዘት በኦሮሞ ህዝብ እውቀት፣ ባህልና ወግ ላይ ያተኮረ ነው። በዚህ ፊልም ከ100 በላይ ባለሙያዎች መሳተፋቸው የተገለጸ ሲሆን በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች ይታያል ተብሏል፡፡

የቴአትር መርሃ ግብር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና አሁድ ከሚታዩ ቴአትሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ ባሎች እና ሚስቶች የተሰኘው ቴአትር ቅዳሜ 8:00 ሰዓት እንዲሁም 11፡30 ደግሞ ባቡሩ የተሰኘው ቴአትር በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይታያል፡፡ እሁድ በ8፡00 ሰዓት ሸምጋይ ቴአትር ለእይታ የሚቀርብ ሲሆን እምዬ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ በብሔራዊ ቴአትር 11፡30 ሰዓት ላይ ይታያል፡፡ እንዲሁም በቀጣይ ቀናት ደግሞ ሐሙስ ቀን 11:30 ሰዓት ጎዶ’ን ጥበቃ በብሔራዊ ቴአትር፣  አርብ በ12፡00 ሰዓት ዋዋጎ በዓለም ሲኒማ፣ አርብ በ11፡30 የሕይወት ታሪክ በብሔራዊ ቴአትር ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review