የመዲናዋ የቱሪዝም እርካቦች

በአዲስ አበባ የተገነቡትና እየተገነቡ ያሉት ፕሮጀክቶች የመዲናዋን ብቻም ሳይሆን የኢትዮጵያን ገጽታም የሚያሳድጉ ናቸው። የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን እንደ ስሟ ውብና አዲስ ማድረግን፣ ከአፍሪካ ዋና ዋና ከተሞች ተርታ እንድትሰለፍ እንዲሁም ለነዋሪዎቿም ሆነ ለጎብኚዎቿ ምቹ መሆንን ያለመ ነው፡፡

እንደ ሀገርም ሆነ ከተማ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የነበረው የግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም አጥጋቢ አልነበረም፡፡ በእጅጉ የተጓተተ፣ ለነዋሪዎች ያለው ምቾትም እምብዛም ነበር። አሁን ይህ ሁሉ ታሪክ ሆኗል፡፡ የቆሻሻ መድፊያና ለማለፍ አፍንጫን የሚሰነፍጡ የነበሩ አካባቢዎች ገጽታቸው ተቀይሯል። የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ እንጦጦ ፓርክ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች የተሰሩ የኮሪደር ልማቶች የዚህ ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው። “በአንድ ጠጠር ሁለት ወፍ” እንዲሉ ከምቹነት ባለፈ የመዝናኛና የቱሪስት መዳረሻም ሆነዋል። አላፊ አግዳሚውን አጃኢብ የሚያሰኙ፣ እጅን በአፍ ላይ እንዲጭኑ የሚያስገድዱም ናቸው፡፡   

“ከተማዋ የሚመጥኑ የመዝናኛ  ቦታዎች ሳምንቱን በሙሉ በስራና በትምህርት ያሳለፉ የማህበረሰብ ክፍሎች አዕምሯቸውን ያሳርፉባቸዋል፤ ይጎበኟቸዋል፤ ይዝናኑባቸዋል” ሲል የፕሮጀክቶቹ መገንባት ደስታን እንደፈጠረለት የሚናገረው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ኤርሚያስ ለማ ነው፡፡ ተማሪ እያለ ትምህርት ቤት ሲዘጋ ወደ መዝናኛ ቦታዎች የመሄድ ልምድ አለው። ቅዳሜና እሁድን  እንዲሁም ክረምት ሲሆን ለመዝናናት ቀኖቹን በጉጉት ይጠብቃቸው እንደነበርም ነግሮናል፡፡

መዲናዋ በቱሪዝም ልማት ላይ እያደረገች ያለው ስራ አበረታች ውጤት እያመጣ ነው

“በሦስትና አራት ዓመታት በፊት በኮሪያ ዘማቾች መናፈሻ ፓርክ፣ አንዳንድ ጊዜም አንበሳ ግቢ እዝናና ነበር፡፡ አሁን ደግሞ አዳዲስ የተገነቡትን አንድነትና እንጦጦ ፓርኮችን ጎብኝቻለሁ፡፡ በጣም ደስ ይላሉ፤ መንፈስንም ያድሳሉ፡፡ እነዚህን ቦታዎች አይቶ የማይደነቅና ራሱን የማያዝናና የለም፡፡ የተሰሩ ፕሮጀክቶች ለከተማዋ ድምቀት ከመሆን በተጨማሪ ለማህበረሰቡም  በንፁህ ቦታ እንዲንቀሳቀስ እንዲሁም ራሱን ካላስፈላጊ ጭንቀትና ድብርት እንዲያወጣ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ከሃገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በሚመጡ ጎብኚዎች በኩል ገቢን ያስገኛሉ። የከተማዋ ነዋሪዎች እየመጡ እዚህ ቢዝናኑ በእድሜያቸው ላይ እድሜን ይጨምርላቸዋል” ሲል ወደፊትም ራሱን በተሰሩት የቱሪስት መዳረሻዎች እንደሚዝናና የከተማዋን መልከ ብዙ ገፆች እየተዟዟረ እንደሚጎበኝ ነው የተናገረው፡፡ 

ሌላኛዋ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ጉብኝት ሲያደርጉ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሳራ  ምትኩ ይባላሉ፡፡ ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው በመዝናናት ላይ ነበሩ፡፡ ልጆቹ ለእናታቸው በጣታቸው እያመለከቱ “ይሄ ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ይጠይቃሉ፤ በደስታ ይቦርቃሉ፤ በጋራ ፎቶ ይነሳሉ፡፡ ለተመለከታቸው ደስታቸው ወደር አልባ ነው፡፡  

ወይዘሮዋ በሰጡት አስተያየት፤ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት አዲስ አበባ የነበራት ገጽታ ምን ይመስል እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። የከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች ገጽታዋን በሚያጎድፍ መንገድ በቆሻሻ ተውጠው ማየት የተለመደ ነበር። አብዛኞቹ እነዚህ ስፍራዎች አሁን ላይ ያሉበት ሁኔታ ለብዙዎቻችን አስደማሚ ነው።

እነዚህ የመናፈሻና የመዝናኛ ቦታዎች እንዲሁም የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ አዕምሮን የሚያድሱና የከተማ አስተዳደሩ አመራር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የውጭ ጎብኚዎችን ቀልብ የሚገዛና የቆይታ ጊዜያቸውንም የሚያራዝም ነው ብለዋል፡፡

የውጭ ሀገራት ዜጎች በእንጦጦ ፓርክ ተገኝተው ሲጎበኙ ተመልክቻለሁ፡፡ ይህ የሆነው የቱሪስት መዳረሻዎች መሰራታቸውን ተከትሎ ነው፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያም በዚህ ልክ የሚገለጽ ሌላኛው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ መታሰቢያ ታሪክን በተጨባጭ የሚያሳይና የሚያሳውቅ ጭምር ነው፡፡  

ወይዘሮዋ በማጠቃለያቸው እነዚህ ለትውልድ የሚተላለፉ መሰረተ ልማቶች   መገንባታቸው አዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ያላቸው እገዛ ትልቅ ነው ብለዋል፡፡

ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ሀሳባቸው ከላይ ከተጠቀሰው የተለየ አይደለም፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ገጽታን የሚገነባ ብቻም ሳይሆን ለቱሪዝም ዘርፉም አቅም የሚሆኑ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የተለያዩ አካላት ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

አቶ ሳምሶን አየናቸው በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና የሃገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፋት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በከተማዋ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ረገድ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ላይ በሰጡን  ማብራሪያ፤ ከዚህ በፊት ከተለያዩ ሃገራት የሚመጡ ዜጎች አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ በቀጥታ የሚሄዱት ኢትዮጵያ ወዳስመዘገበቻቸው የቱሪዝም ቦታዎች ነበር። አሁን ላይ በመንግስት ጥረት የመዳረሻ ልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት  ከዓለም አቀፍ የቱሪስት ፍሰት ድርሻ ተጠቃሚ ለመሆን በዘርፉ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ 

በዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የአንድነት፣ እንጦጦ፣ የወዳጅነት አደባባይ ፓርኮች፣ የሳይንስ ሙዚየም ተገንብተዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን እንደ ሆቴል ያሉ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትንም ጭምር ተወዳዳሪ የማድረግ ስራዎች በመስራትና በነባር የመስህብ  ቦታዎች ላይ እሴቶችን በመጨመር ሳቢና ማራኪ በማድረግ ከተማዋን ከመሸጋገሪያነት ወደ መዳረሻነት መቀየር ተችሏል፡፡

የኮሪደር ልማቱ እንዲሁ የአዲስ አበባን ውበት በማጉላት፣ ገፅታዋን በማሻሻል፣ ለነዋሪዎቿና ለእንግዶቿ ምቹ እንድትሆን በማድረግ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ መሰል ከተሞች ጋር ያላትን ተወዳዳሪነት በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ስለመሆኑ ነው አቶ ሳምሶን የተናገሩት፡፡

በከተማዋ ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ከማልማትና ከመጠበቅ ባሻገር የማስተዋወቅ ተግባር በእጅጉ አስፈላጊ ነው የሚሉት አቶ ሳምሶን፤ በዚህ ረገድ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንን በተለየ ሁኔታ ደግሞ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በFM 96.3 በቋሚነት በየሳምንቱ የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡

አቶ ሳምሶን አክለውም፤ ከተማዋን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ያሳያል፡፡ ለአብነትም በ2015  በጀት ዓመት ከ3 ሚሊዮን 70 ሺህ በላይ በተለያየ ምክንያት መጥተው ከተማዋን የጎበኙ የሀገር ውስጥ እና ከ391 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች ከተማዋን ጎብኝተዋል፡፡ በ2016 በጀት ዓመት ከ9 ሚሊዮን 105 ሺህ በላይ የሃገር ውስጥ እና 950 ሺህ የውጭ ሃገራት ዜጎች አዲስ አበባን ጎብኝተዋል፡፡ በ2017 በጀት ዓመትም 9 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ እና አንድ ሚሊዮን የውጭ ሀገር ዜጎች ከተማዋን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

 በከተማዋ ያለውን የቱሪዝም እድገት ለማሳደግ ከገበታ ለሸገርና ከገበታ ለሃገር በተጨማሪ ወደፊት ገበታ ለትውልድ በሚል በሃገር አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም ስራዎች ለማከናወን በእቅድ መያዙን የሚገልጹት አቶ ሳምሶን፤ እንደ ከተማ ባሉት የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ እሴት በመጨመር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ከመሸጋገሪያነት ወደ መዳረሻነት መለወጧን የሚያረጋግጡት ደግሞ በቢሮው የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃፍታይ ገብረእግዚአብሔር ናቸው። የኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት “የአፍሪካ ከተሞች 2035” በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርት አዲስ አበባ  እ.ኤ.አ በ2035 ከ6ቱ የአፍሪካ ሜጋ ከተማዎች አንዷ እንደምትሆን ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት ጠቅሷል፡፡ የዚህም ምክንያት ከተማዋ ለቱሪዝም ትኩረት መስጠቷ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ትላልቅ መሰረተ ልማቶችና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች በመገንባታቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከተማዋ የምትወቀስበትን የውበትና ፅዳት ጉድለት ምላሽ እየሰጠ ያለው የኮሪደር ልማት ዓለም አቀፍ እንግዶች ቀን ቆርጠው የመጡለትን ስብሰባ፣ ኮንፈረንስ እና መሰል ሁነት ባጠናቀቁ ማግስት ወደመጡበት ከመመለስ ይልቅ በመዲናዋ የሚያደርጉትን ቆይታ እንዲያራዝሙ በሚያደርግ መልኩ የጎብኚዎችንም ቀልብ የሚስቡ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ይህም የመዲናዋን ገፅታ በመሰረታዊነት እየለወጠ እና ዘመናዊነቱን ከፍ እያደረገ ነው። የትራፊክ ፍሰቱ የተሳለጠና የነዋሪዎችም ጤና እንዲጠበቅ የኮሪደር ልማቱ አስተዋፅኦው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ 

በከተማዋ የተገነቡትን የቱሪስት መዳረሻዎች በማስተዋወቅ ረገድም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ዓለም አቀፍ መድረኮች ሁሉ የማስተዋወቅ ስራ እየሰሩ ነው፡፡ በተጨማሪም እንደ ከተማ በየአደባባዮቿ ከተማዋን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በመጠቀም እያስተዋወቅን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“በቀጣይም የከተማዋን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ቁጥር በመጨመርና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱን በማሻሻል አዲስ አበባ ከዘርፉ በሚፈለገው ልክና ደረጃ እንድትጠቀም፣ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል” ያሉት አቶ ሃፍታይ፤ ለዚህም  የከተማዋን የቱሪዝም መስህቦች ለማስተዋወቅ አርቲስት መቅደስ ጸጋዬን የቱሪዝም አምባሳደር አድርገን በመሾም እየሰራን እንገኛለን፡፡ አርቲስት መቅደስም ከዚህ ቀደም የቱሪዝም አምባሳደር ሆና በተሾመችበት ወቅት እና በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ “በእኔ አይን” ፕሮግራም ላይ እንደተናገረችው ትልቅና ታሪካዊ የሆነችውን የአዲስ አበባ ከተማን ማስተዋወቅ ትልቅ ዕድልና ክብር ነው፡፡ አዲስ አበባ በርካታ ተጎብኝተው የማያልቁ የታሪክ፣ የባህልና ቅርስ ሀብት ያላት ከተማ ናት ማለቷ ይታወሳል። የተሰራውን ስራ ከማስተዋወቅ በተጨማሪ በቱሪስት መዳረሻዎች ላይ ጎብኚዎች ምን ያህል ደስተኛ ናቸው? የሚለውን በመገምገም ጉድለቶች ካሉ ለማስተካከል ተዘጋጅተናል ሲሉ ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት አብራርተዋል፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review