የመዲናዋ የአምስት ዓመታት ኢኮኖሚያዊ ፍሬዎች

You are currently viewing የመዲናዋ የአምስት ዓመታት ኢኮኖሚያዊ ፍሬዎች

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲና ናት። ከዚህ በተጨማሪም አፍሪካውያን “ቤቴ” የሚሏት፣  ከኒው ዮርክና ጀኔቫ በመቀጠል ሦስተኛዋ የዓለም የዲፕሎማሲ ከተማም ነች፡፡ በሀገር አቀፍ፣ በቀጣናው፣ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ሚና የምትጫወተው አዲስ አበባ  የከተማነት ደረጃዋ ይህን ስሟን የሚመጥን አልነበረም፡፡ ብዙ ሰፈሮቿ በእርጅና የተጎሳቆሉ፣ መንገዶቿ ከመጀመሪያውም ሲገነቡ ተሽከርካሪን ብቻ ታሳቢ ያደረጉ፣ በጥራት፣ በዘመናዊነትም ሆነ በሽፋን ደረጃዋን የሚመጥኑ አልነበሩም። የምትሰጣቸው የትራንስፖርት፣ የጤና፣ የስራ ዕድል፣ የትምህርት፣ የመዝናኛ እና መሰል የህዝብ አገልግሎቶችም እንዲሁም በርካታ ችግሮች ያሉባቸው ሆነው ቆይተዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም የመጣው ሀገራዊ ለውጥ ለአዲስ አበባ ከተማ እድገት ትልቅ ተስፋን የፈነጠቀ ነው፡፡ ለውጡን ተከትሎ በሁለንተናዊ መልኩ ውጤት አምጥታለች፡፡ ምንም እንኳን በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮቪድ- 19 ወረርሽኝ እና በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የዓለም ንግድ መዛባትን ተከትሎ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ቢስተዋልም፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ ግጭቶች፣ ድርቅ እንዲሁም ስራ አጥነት ያሉ ውስብስብ ችግሮች ቢያጋጥሙም ባለፉት አምስት ዓመታት አመርቂ የሚባሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

ውጤት ከተገኘባቸው ዘርፎች መካከል ኢኮኖሚው ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ መስክ የከተማዋን ውበትና ገፅታ የቀየሩና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ያሳደጉ በርካታ ልማቶች ተከናውነዋል፡፡  መልክና ገፅታ ከቀየሩ ትላልቅ ልማቶች መካከል በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አፍላቂነት ተገንብተው ለህዝብ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆኑት የአንድነትና እንጦጦ ፓርኮች፣ ወዳጅነት አደባባይና የሳይንስ ሙዚየምን መጥቀስ ይቻላል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ የሀገሪቱ መሪዎችና የከተማ አስተዳደሩ አመራር መዲናዋን ለመለወጥና ህይወት ያለው የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ እንዲኖር ለማድረግ ከሌሎች ሀገራት ትላልቅ ከተሞች ጋር ትስስር በመፍጠር ያደረጓቸው ጥረቶች የሚደነቁ ናቸው፡፡ የመዲናዋ ነዋሪዎችና ዲፕሎማቶች ለመኖር፣ ለመገናኘት፣ ለመሰባሰብ እንዲሁም ለመዝናናት የህዝብ መናፈሻና መዝናኛ ቦታዎች ወሳኝ ናቸው። በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት የተሰሩ ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከዚህ ቀደም እንደተናገሩት፣ በከተማዋ የተገነቡ ፓርኮች አዲስ አበባን ተወዳዳሪ እያደረጉና የውጭ ምንዛሬ ችግር የመፍቻ ቁልፍ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በከተማዋ እውን ከሆኑ ፕሮጀክቶች መካከል በዓድዋ ጦርነት የተሳተፉ ጀግኖችንና የጋራ የሆነውን ድል ለመዘከር የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ተጠቃሽ ነው፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጉቱ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ መታሰቢያው የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴውን በማነቃቃትና ማህበራዊ መስተጋብርን በማጠናከር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ነው፡፡

በውስጡ ብዙ ታሪኮችን የያዘ በመሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች የሚጎበኙት፣ የኢትዮጵያ ገጽታ የሚገነባበትና ገቢ የሚገኝበት የቱሪስት መስህብ ስፍራ ነው፡፡ በመታሰቢያው በሚገኙ የተለያዩ ክፍሎች እየተደረጉ ያሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ለከተማዋ ምጣኔ ሀብት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ትላልቅ የስብሰባ አዳራሾች፣ የኤግዚቢሽን ማዕከላት፣ ሲኒማ ቤቶች ከዚህ በፊት እንደ ሚሊኒዬም አዳራሽ፣ ኤግዚቢሽን ማዕከልና ሌሎች የስብሰባ ማዕከላት ይደረጉ የነበሩ ኹነቶችን በተሻለ ጥራት ለማስተናገድ የተመቹ በመሆናቸው በኪራይ ብዙ ገቢ ማመንጨት ያስችላሉ፡፡

ከዚህ ባሻገር መታሰቢያው በከተማዋ ማዕከላዊ አካባቢ የተሰራ በመሆኑ በተለያዩ ርቀት የሚኖሩ ነዋሪዎች በትርፍ ጊዜያቸው ወደ አካባቢው በመምጣት የሚዝናኑበት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ የውጭ ሀገር እንግዶችም መታሰቢያውን ሲጎበኙ የሚገኘው ገቢም የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይደግፋል፡፡ ከግንባታው ጀምሮ ተቋራጮችን፣ አማካሪዎችን፣ ሰራተኞችን፣ የተለያየ ግብዓት አቅራቢዎችን… ተጠቃሚ አድርጓል። ወደፊትም ለከተማዋ ትልቅ የምጣኔ ሀብት አንቀሳቃሽ መሆን የሚችል የቱሪዝም መስህብ ነው ሲሉ አብራርተዋል።ሌላኛው ባለፉት ዓመታት የከተማ ገፅታ እየቀየሩ ካሉ ስራዎች መካከል በጉልህ የሚጠቀሰው የኮሪደር ልማቱ ነው፡፡ ልማቱ የተሽከርካሪ እና እግረኛ መንገዶችን የማስፋት፣ የአረንጓዴ ስፋራዎችን ሽፋን፣ የሳይክል መንገዶችን የማስፋት፣ የውሃ ፍሳሽና የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ደረጃ የማሳደግ፣ ህንፃዎች ተመሳሳይ ስታንዳርድ እንዲይዙ ማድረግን ያካተተ ነው። “የኮሪደር ልማቱ በአዲስ አበባ ውበት፣ ጽዳትና ገፅታ ላይ ያመጣውን ውጤት ማንም የሚክደው አይደለም፡፡ የሚያማምሩ ጎዳናዎች ካላቸው ከተሞች ተርታ የሚያሰልፋት፣ ሰዎች የአካል እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ፣ ከአየር ብክለት ነፃ የሆኑ የትራንስፖርት መጓጓዣዎችን እንዲጠቀሙ፣ የሚታዩ፣ መንፈስና አዕምሮ የሚያድሱ፣ ደስታን የሚጨምሩ ነገሮች የተሰሩበት ነው፡፡ ውብና ፅዱ አካባቢ፣ ጤናማ ማህበረሰብ በመሳብ፣ ቱሪዝምን በማሳደግ ትልቅ ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ አለው” ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጉቱ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡ 

ሌላው እንደ ሀገርም ሆነ ከተማ ፈተና የሆነው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከዚህ ቀደም ለዝግጅት ክፍላችን የሰጠው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ለችግሩ መባባስ አንደኛው ምክንያት ረጅም የገበያ ሰንሰለትና እሴት የማይጨምሩ ደላሎች መኖር ነው፡፡ አርሶ አደሩ ከማሳው የሚሸጥበት ዋጋ እና ምርቱ በከተሞች ለሸማቹ በሚሸጥበት ዋጋ መካከል ከፍተኛ ልዩነት ይታያል፡፡ በዚህም የተነሳ አምራቹና ሸማቹ እየተጎዳ ደላሎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት አካሄድ ነበር፡፡

ይህን ምርቶች ከተለያዩ አካባቢዎች መጥተው ሸማቹ ጋር እስኪደርሱ ድረስ ያለውን የተንዛዛና እሴት የማይጨምር ይልቁንም ለዋጋ ንረት ምክንያት የሆነ የደላላ ጣልቃ ገብነት ለመከላከል፣ አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ በከተማዋ ዋና ዋና መግቢያ በሮች የግብርና ምርቶች ማከፋፈያና መሸጫ የገበያ ማዕከላት ተገንብተዋል፡፡ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 አያት፣ ወረዳ 5 ሰሚት እንዲሁም ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ቤተል የተገነቡ ግዙፍ ማዕከላት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ጉቱ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ የተገነቡ የገበያ ማዕከላት የዋጋ ንረትን በማርገብ ትልቅ አስተዋፅኦ ያላቸው ናቸው፡፡ ከዓመታት በፊት በከተማዋ የነበረው የአትክልትና ፍራፍሬ መገበያያ ስፍራዎች ቁጥር በጣም አናሳና የከተማዋን ነዋሪዎች የማይመጥኑ ነበሩ። ብዙ ግብይት የሚካሄድበትም ፒያሳ አካባቢ የሚገኘው በተለምዶ አትክልት ተራ እየተባለ የሚጠራው ስፍራ ነበር፡፡ ገበያው ብቸኛ ከመሆኑ አኳያ ግብይቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ ነበር፡፡ በቅርብ ዓመታት በተለያዩ የከተማዋ መግቢያና መውጫ በሮች የተገነቡ የገበያ ማዕከላት ለተጠቃሚው የግብርና ምርቶችን በየአካባቢው በወቅቱ ለማግኘት የሚያስችሉ ናቸው፡፡ ሸማቹ ረጅም ርቀት ተንቀሳቅሶ የመጓጓዢያ ወጪ ተጨምሮበት በውድ ዋጋ የሚገዛበትን ሁኔታ በማስቀረት በአካባቢው በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ አስችለዋል፡፡

የገበያ ማዕከላት ምርቶችን ከማቅረብ በተጨማሪም ለበርካታ ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ማህበረሰቡ ትኩስ ምርቶችን እንዲያገኝ እንዲሁም መንግስትም ስርዓቱን ጠብቆ ከሚካሄደው ግብይት ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ያግዛሉ፡፡

ሌላው የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ የተወሰደው እርምጃ በመዲናዋ ለሚገኙ የሸማች ህብረት ሥራ ማኅበራት የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦት ማመቻቸት ነው፡፡ የምርት አቅርቦትን በማሳለጥና የገበያ ተደራሽነትን በማረጋገጥ የሸማች እና ህብረት ስራ ማህበራት ትልቅ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን በመገንዘብም የፋይናንስ አቅማቸውን በማጎልበት ለከተማዋ የሚያቀርቡትን ምርት ለማሳደግ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ በማመቻቸት ሰፊ የሆነ የሰብል ምርቶችን እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡

የከተማዋ አካባቢዎች አምራችና ሸማቹ የሚገናኙባቸው እሁድ ገበያዎችን በማቋቋም፣ ከመደበኛው የገበያ ዋጋ ባነሰ በተመጣጣኝ ዋጋ ለነዋሪዎች እንዲያቀርቡ የተደረገበት መንገድም ሌላኛው ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም፣ መንግስትም በተደጋጋሚ ጊዜ እንደሚናገሩት ለዋጋ ንረትና ለኑሮ ውድነት መባባስ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው በምርት ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለው አለመመጣጠን ነው። ከዚህ አኳያ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ባለፉት ዓመታት እንደሀገር በስንዴ፣ ሩዝ፣ በከተማ ግብርና፣ የሌማት ትሩፋት (እንቁላል፣ ወተት፣ ስጋና ማር…) ስራዎች ርብርብ በማድረግ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡

እንደ ከተማ ስንመጣም በብዙ የዓለም ሀገራት ከተሞች የከተማ ግብርናን በመተግበር 20 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚሆነውን የምግብ አቅርቦታቸውን ይሸፍናሉ፡፡ ይህንን ተሞክሮ በመውሰድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ስር በአንድ ዳይሬክቶሬት ይመራ የነበረውን የከተማ ግብርና ራሱን ችሎ ተደራጅቶ እንዲወጣ አድርጓል፡፡ ይህም ዘርፉን ከማሳደግ አኳያ ትልቅ እርምጃ ሲሆን፤ በተለያዩ የጓሮ አትክልት፣ የስጋና እንቁላል ዶሮ፣ ወተትና ማር ምርቶች በልዩ ሁኔታ በመስራቱ ውጤታማ መሆን ተችሏል፡፡ 

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጉቱ (ዶ/ር) እንደሚገልፁት፤ የከተማ ግብርና የኑሮ ውድነትን ለማርገብ፣ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተስማማ ልማት ለማምጣት፣ የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ ትኩስና

ጤናማ የግብርና ምርት ፍጆታዎችን ለማቅረብ ትልቅ አቅም አለው፡፡ እንደነ ታይላንድ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና የመሳሰሉ የእስያ ሀገራት ከተሞች የምግብ ዋስትና ችግርን ለማቃለል ተጠቅመውበታል። በአዲስ አበባ ከተማም ከዚህ አኳያ የተከናወኑ ስራዎች ፋይዳቸው ከፍ ያለና ሊበረታቱ የሚገቡ ናቸው፡፡

ሚያዝያ 12 ቀን 2015 ዓ.ም፤ “ምክንያታዊ ወጣት ለአዲስ አበባ ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ በሚሊኒዬም አዳራሽ በተካሄደውና ከ16 ሺህ በላይ የመዲናዋ ወጣቶች በተሳተፉበት መድረክ ላይ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፣ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በከተማዋ የሰውን ህይወት የሚቀይሩ በርካታ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

“አዲስ አበባ ላይ የብዙ ጎስቋላ አካባቢዎች ገፅታ ተቀይሯል፤ በቅድሚያ የተቀየረው ግን የሰው ህይወት ነው፡፡” ያሉት ከንቲባዋ፣ ከ700 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የምገባ ተጠቃሚ በማድረግ፣ ምንም ዓይነት አቅም የሌላቸው ዜጎች ምግብ በነፃ የሚመገቡባቸው የምገባ ማዕከላት በማስፋፋት፣ የበርካታ አቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ የተሰሩ ስራዎችን በወቅቱ ለአብነት ጠቅሰዋል።

ሌላው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ህይወት ለማቃለል የተሰሩ ስራዎችን ስናነሳ የዳቦ ፋብሪካዎች ግንባታን አብሮ መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ የከተማ ነዋሪው በየአካባቢው በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ የሚያገኝበትን ሁኔታ በመፍጠር የኑሮ ጫናን ለመቀነስ መንግስት ከግል ባለሀብቶች ጋር አጋርነት በመፍጠር በርካታ የዳቦ ፋብሪካዎችን ገንብቷል፡፡ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ባሉት ዓመታት በአዲስ አበባ በቀን እስከ 300 ሺህ ዳቦ ይመረት ነበር። ዛሬ ላይ በቀን በሚሊዮን የሚቆጠር ዳቦ ማምረት የሚቻልበት አቅም ተፈጥሯል፡፡ ይህም የሚበረታታ ተግባር እንደሆነ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጉቱ (ዶ/ር) አንስተዋል፡፡

ዘመናዊ አዳዲስና ነባር መንገዶችን የመገንባትና የመጠገን ስራ ተሰርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የመስቀል አደባባይ፣ የቤተ መንግስት የመኪና ማቆሚያ፣ የአብርሆት ቤተ መጻህፍት ፕሮጀክት በጥቅሉ ዘርዝረን የማንጨርሳቸው ፕሮጀክቶች ተሰርተዋል፤ እነዚህ ደግሞ ለከተማዋ ብዙ ነገር አስገኝተውላታል፡፡ የጉብኝት ማዕከል እና ደረጃዋን የጠበቀች የዓለም አቀፍ የኮንፈረንስ ማዕከል እንድትሆን አግዟታል፡፡ ከቱሪስት መሸጋገሪያነት ወደ መዳረሻነት ለውጠዋታል፡፡ 

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጉቱ (ዶ/ር) አዲስ አበባ ካላት የገዘፈ ሚና አኳያ የኢኮኖሚ ልማቷና የምትሰጠው አገልግሎት የሚመጥናት ሳይሆን ቆይቷል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተሰሩ ስራዎች የሚደነቁና ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ስሟን እና ሚናዋን የምትመጥን ከተማ እንድትሆን በቀጣይ የኑሮ ውድነትን በማርገብ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በሰላምና መረጋጋት ላይ አበክራ መስራት ይጠበቅባታል። በሌሎች አካባቢዎች ያሉ የሰላም ችግሮች በከተማዋ ሰላምና ፀጥታ ላይ የራሳቸው የሆነ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ስላላቸው በዚህ ረገድ የሚሰሩ ስራዎችም ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ልማት ረገድም ከተማዋ ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች የሚሆኑ ጥራት ያላቸው የኢንዱስትሪ ምርቶች በብዛት ማቅረብ ያስፈልጋል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን አብዛኛው ከውጭ የሚገቡ ናቸው፡፡ በማህበራዊ ልማት ረገድም ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን የሚመጥን የትምህርት፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የጤናና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማቅረብ መስራት ይጠበቅባታል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጉቱ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ሀገሪቱ እንደ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ጦርነት… ያሉ ውስብስብ ፈተናዎች ውስጥ በሆነችበት የተገኙ ስኬቶች የሚበረታቱ ናቸው፡፡ አዳዲስና ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የቆዩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ፣ መንገዶችን በማሳመርና ለአገልግሎት ምቹ እንዲሆኑ በማድረግ የተሰሩ ስራዎች የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴን በማሳለጥ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ናቸው፡፡

በጥቅሉ ባለፉት አምስት ዓመታት አዲስ አበባን ልዩ ውበትና ገጽታን ያላበሱ፣ እድገቷን የሚያፋጥኑ፣ የቱሪዝም መስህብ በመሆን ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ፣ የነዋሪዎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያሳደጉ ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ተምሳሌት የሆኑ የልማት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ እነዚህን ስራዎች በማስፋት፣ ያሉትን በማስተዋወቅና በመጠበቅ የከተማዋን ልማት ማፋጠን ይገባል እንላለን፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review