የመዲናዋ የውበት ምንጭ

You are currently viewing የመዲናዋ የውበት ምንጭ

በከተማዋ እየተሰራ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ፣ ብዙሃን የሚጠቀሙበትን የእግረኛ መንገድ ማስፋትና ምቹ ማድረግ፣ የተሽከርካሪ መንገዶችን ማስፋት፣ የአስፋልት መንገዶች ማደስ፣ አላስፈላጊ የመንገድ ማካፈያዎችን አንስቶ መንገዱን ማስፋት፣ የመኪና ማቆሚያዎችን የመስራት፣ የመንገዶችን ዳር ማሳመር፣ የቴሌና የመብራት ኬብሎችን በመሬት ውስጥ እንዲያልፉ ማድረግ፣ ዘመናዊ የውሃ ፍሳሽ መሄጃዎችን፣ የሳይክል መንገድ፣ ፕላዛዎችን በመስራት ከተማዋን ለኑሮ የተመቸች ማድረግ ነው ዓላማው። አብሮም ደረጃቸውን የጠበቁ መጸዳጃ ቤቶች እየተሰሩ ሲሆን፣ ይህም ለመዲናዋ አዲስ ገፅታን ያላበሰ እንደሆነም ብዙዎች በመመስከር ላይ ናቸው፡፡

ስራዎቹ በሳምንት 7 ቀን ለ24 ሰዓት (ቀን እና ማታ) እየተሰሩ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ህንጻዎችን የማደስ፣ ወደ ንግድ ማዕከልነት የመቀየር እና በስታንዳርድ የተቀመጠውን መስፈርት (የህንጻዎች ቀለም ጭምር) እንዲያሟሉ እየተደረገ ነው።

አዲስ አበባ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች፣ ቆንስላዎችና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ መቀመጫ ናት፡፡ ታዲያ ይህን ሚና የያዘች ከተማ ብትሆንም እንደ እድሜዋ ያልዘመነች፣ ለነዋሪዎች ምቹ ያልሆነች ከተማ እየተባለች ትተቻለች፡፡ ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት የከተማ አስተዳደሩ በኮሪደር ልማት አዳዲስ ለውጦችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡

የኮሪደር ልማቱ መንግሥት አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ ለማድረግ ቀደም ሲል የገባውን ቃል መሠረት አድርጎ እየሰራ እንደሆነም አሳውቋል። ለዚህ ደግሞ ፒያሳና አራት ኪሎ እንዲሁም የኮሪደር ልማቱ የጎበኛቸው ስፍራዎች ምስክር ናቸው፡፡

እየተፋጠነ የሚገኘው 2ኛው ዙር የኮሪደር ልማት በለገሃር አካባቢ

በመጀመሪያ ዙርም በዓድዋ ድል መታሰቢያ አካባቢ፣ ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ፣ ከቀበና እስከ መገናኛ፤ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ አየር ማረፊያ፣ ከቦሌ ድልድይ እስከ መገናኛ፣ ከመገናኛ እስከ አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከል (ሲኤምሲ) እንዲሁም ከሜክሲኮ እስከ  አፍሪካ ኅብረት ሳር ቤት ወሎ ሰፈር የኮሪደር ልማት ሥራ ተከናውኗል፡፡

የከተማዋን ነባር አካባቢዎች የሸፈነው የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት አምስት መስመሮችን የያዘ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚህም ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ቦሌ፣ መገናኛ፣ ሜክሲኮ እና ሲ.ኤም.ሲ ሲሆኑ ለከተማዋ አዲስ ገፅታን አላብሰዋል፡፡

ሰሞኑን የከተማ አስተዳደሩ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ የሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሽፋን፣ ካዛንቺስ፣ መስቀል አደባባይ፣ ሜክሲኮ፣ ቸርችል፣ አራት ኪሎ፣ እስጢፋኖስ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት 1 ሺህ ሄክታር ቦታ ስፋት እና 40 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ርዝመት፣ ሳውዝጌት፣ መገናኛ፣ ሃያ ሁለት፣ መስቀል አደባባይ የኮሪደር ልማት 128 ነጥብ 7 ሄክታር የቦታ ስፋት እና 7 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ርዝመት፣ ሲ.ኤም.ሲ፣ ሰሚት ጎሮ፣ ቦሌ አየር ማረፊያ ቪአይፒ ተርሚናል፣ አዲስ አፍሪካ አለም አቀፍ ኮንቬንሽንና ኤግዚብሽን ማዕከል የኮሪደር ልማት 146 ሄክታር የቦታ ስፋት እና 10 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት፣ ሳር ቤት፣ ካርል አደባባይ፣ ብስራተ ገብርኤል፣ አቦ ማዞሪያ፣ ላፍቶ አደባባይ፣ ፉሪ አደባባይ ኮሪደር ልማት 565 ሄክታር የቦታ ስፋት እና 15 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው፡፡

ሌላው አንበሳ ጋራዥ፣ ጃክሮስ ጎሮ ኮሪደር ልማት 16 ነጥብ 58 ሄክታር የቦታ ስፋት እና 3 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ርዝመት፣ አራት ኪሎ፣ ሽሮ ሜዳ እንጦጦ ማርያም፣ ጉለሌ እጸዋት ማዕከል የኮሪደር ልማት 314 ሄክታር የቦታ ስፋት እና 13 ነጥብ 19 ኪሎ ሜትር ርዝመት፣ የቀበና ወንዝ ዳርቻ ኮሪደር ልማት 372 ነጥብ 5 ሄክታር የቦታ ስፋት እና 20 ኪሎ ሜትር ርዝመት፣ እንጦጦ፣ ፒኮክ ፓርክ የወንዝ ዳርቻ ልማት ኮሪደር ልማት 274 ሄክታር የቦታ ስፋት እና 21 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲሆን በአጠቃላይ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት 2 ሺህ 817 ሄክታር የቦታ ስፋት እና 132 ኪሎ ሜትር ርዝመትን ይሸፍናል ብሏል።

ሜክሲኮ አካባቢ ያገኘናቸው የመዲናዋ ነዋሪ አቶ አንጋሳ በሀብቱ እንደሚሉት የኮሪደር ልማቱ የአዲስ አበባ ከተማን ታላቅነትና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪ ከተማ እና ስሟን የሚመጥን ለማድረግ እንዲሁም ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የተጀመረ በመሆኑ የሚያስደስት ነው፡፡ በተለይም ከሜክሲኮ እስከ መስቀል አደባባይ ያለው መስመር የመዲናዋ ታላላቅ ተቋማት ያሉበት፣ በርካታ እንቅስቃሴ ያለበት ስፍራ በመሆኑ የመዲናዋን ገፅታ የበለጠ የሚያሳድግ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም ከሜክሲኮ እስከ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ድረስ የሚዘልቀው መንገድ በርካታ የትራፊክ መጨናነቅ የሚስተዋልበት እንደሆነ የነገሩን በታክሲ ሾፌርነት በዚህ አካባቢ ከ10 አመት በላይ እንዳገለገሉ የነገሩን አቶ ምግባሩ ከድር ናቸው። በመኪናዎች ከሚፈጠረው መጨናነቅ ባሻገርም ወደ ሜክሲኮ አካባቢ እግረኛው ከእግረኛ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመኪና ጋርም እየተጋፋ የሚሄድበት፣ መኪና ማቆሚያ ፌርማታ እና የእግረኛ መንገድ እጥረት ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አካባቢው በኮሪደር ልማት እንዲለማ መደረጉ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ምግባሩ ገለፃ የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት መዲናዋን ልዩ ውበት ያጎናፀፈ ከመሆኑ አንፃር በ2ኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስራም በዚህ አካባቢ ትልቅ ለውጥ እንደሚመጣ አሁን ካለው እንቅስቃሴ መረዳት ይቻላል፡፡ በተለይም ይህ አካባቢ ከውጭ ሀገራት የሚመጡ እንግዶች የሚያዘወትሩበት እንደመሆኑ ከገፅታ ግንባታ አንፃር ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነም ከስራቸው ባህሪ አንፃር እንደሚገነዘቡት ነግረውናል፡፡

ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከተማ ዱባይ ጥቂት መሰረተ ልማት ብቻ ያለባት ምድረ በዳ ከተማ ነበረች፡፡ የሚያቃጥል ፀሀይ፣ አሸዋማ መሬት እና ዙሪያዋን የከበባት ውሃ መገለጫዋ ነበር፡፡ በፈረንጆቹ 1966 የነዳጅ ዘይት መገኘት በዱባይ የዕድገት ታሪክ እንደ ወሳኝ ምዕራፍ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይሁን እንጂ ከተማዋ ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በንግድና ቱሪዝም ማዕከልነት በግንባር ቀደምትነት እንድትጠቀስ ያበቃት የወሰደቻቸው በርካታ እርምጃዎች አሉ፡፡ “ሊንክድ ኢን” ገፀ-ድር ላይ “Dubai’s Economic Transformation: A Beacon of Employment and Productivity” በሚል ርዕስ የወጣው ጽሁፍ ላይ እንደሰፈረው ኢኮኖሚውን ከነዳጅ ጥገኝነት የተላቀቀ፣ ሁሉን አቀፍና ብዝሃነት ያለው፣ ምቹ ከባቢ በመፍጠር ለቱሪዝምና ሆቴል፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ከአካባቢ ጋር የሚስማሙና የተጣጣሙ ተነሳሽነቶችን በመተግበር ዘላቂነት ያለው የከተማ ልማትን በማምጣት በዓለም ከፊት የምትጠራ ከተማ ሆናለች፡፡

የአፍሪካ መዲናና የዓለም የዲፕሎማሲ ከተማ የሆነችው አዲስ አበባም ስሟንና ደረጃዋን ወደምትመጥን ከተማ ለማሸጋገር በርካታ ልማቶችን እያከናወነች ትገኛለች፡፡ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ከተማን በፕላን መምራት የግድ ነው። ከተማ በአግባቡ ከተመራ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የቱሪዝም፣ የመዝናኛ በጥቅሉ ምቹ የመኖሪያ ማዕከል ይሆናል፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ የመከራና ስቃይ ቦታ ይሆናል ይላሉ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በከተማ ልማትና ምህንድስና ኮሌጅ የከተማ ዲዛይንና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር)፡፡

 “አዲስ አበባ የነበረችበት ሁኔታ ደረጃዋን የሚመጥን አልነበረም” የሚሉት ዳንኤል (ዶ/ር) የኮሪደር ልማት ብዙ ትሩፋት አምጥቷል፡፡ አንደኛው ትሩፋት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቀላጠፉ ማገዝ ነው፡፡ ከተማዋ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ የሚደረግባት፣ ሁሉንም የምታሳትፍ፣ ኢንቨስትመንት መሳብ የምትችል፣ የመኖሪያ፣ የንግድና የመዝናኛ ከተማ እንድትሆን እያስቻላት ነው፡፡

ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ (Peak Hour) የሚኖረው፤ ሰዎች ወደ ስራ በሚገቡበት እና ከስራ የሚመለሱበት የማታ ክፍለ ጊዜ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን በአዲስ አበባ ሙሉ ቀን የትራፊክ መጨናነቅ የሚታይባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ዳንኤል (ዶ/ር) ያነሳሉ። በዚህም የተነሳ ሰዎች መንገድ ላይ ብዙ ጊዜ ያጠፋሉ፡፡ ጊዜ ማለት ደግሞ ገንዘብ ነው። በኮሪደር ልማቱ እንቅስቃሴው የተሳለጠና ፈጣን ሲሆን በመንገድ መዘጋጋት የሚጠፋው ጊዜ ይቀንሳል፡፡

የትራፊክ ሲስተሙ ዘመናዊ አለመሆኑ፣ ተሽከርካሪዎች ዝግዛግ እየሰሩ የሚሄዱ መሆናቸው፣ በኮሪደር ልማቱ ከባድ መኪና፣ ብረት ላይ የሚሄድ መኪና (ወደፊት የሚኖር)፣ ፈጣን አውቶብስ፣ አውቶሞቢል፣ አምቡላንስ፣ እግረኛውና ሌላውም በራሱ መስመር ብቻ ስለሚንቀሳቀስ የትራፊክ ፍሰቱ የተሳለጠና ፈጣን ይሆናል፡፡ አንዱ ከአንዱ ሳይጋጭ ስለሚሄድ ዘላቂነት ያለው የትራፊክ ፍሰት (Mobility) እንዲኖር ያደርጋል፡፡

ሌላው ጥቅሙ ከተማዋ ውብና አረንጓዴ እንድትሆን ያስችላታል፡፡ ሰዎች ለምንድን ነው ዱባይ፣ ፓሪስ፣ ኬፕ ታውን፣ ራባት፣ ሲቪያ፣ ማላጋ፣ ባርሴሎና… መሄድ የሚፈልጉት? ሲሉ የሚጠይቁት ዳንኤል (ዶ/ር) የሰው ልጅ በተፈጥሮ ውበትን የሚያደንቅ ፍጡር ስለሆነ ነው ብለው ይመልሳሉ፡፡ የኮሪደር ልማት የከተማ ስነ- ውበትን (Aesthetics) ለማምጣት ያስችላል። ይህም የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን ይስባል፡፡

የኮሪደር ልማቱ የአዲስ አበባ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን በማቀላጠፍ፣ ንጹህ፣ አረንጓዴ፣ ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ ልማት ለማምጣት የሚያግዝ ነው፡፡ ከተማዋን በስሟና በሚመጥናት ደረጃ እንድትገኝ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካትም ትልቅ እገዛ የሚያደርግ በመሆኑ ለውጤታማነቱ ሁሉም መረባረብ ይኖርበታል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review