የመዲናዋ የዲፕሎማሲ ክራሞት

አዲስ አበባ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ትልቅ ሚና የምትጫወት ከተማ ናት፡፡ የአፍሪካ ህብረትን እና የተባበሩት መንግስታት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንን ጨምሮ በርካታ ቀጣናዊ፣ አህጉር አቀፍና የአለም አቀ።ፍ ድርጅቶች ማዕከል በመሆኗ የአፍሪካ የፖለቲካ መዲና ነች ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በዓለም ላይም ከኒውዮርክ እና ጀኔቫ በመቀጠል ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል ናት፡፡

ሊገባደድ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀሩት 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ በብዙ መልኩ ለውጥ ያሳያችበትና ስኬታማ የሆነችበት ዓመት ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ስኬታማ ከሆነችባቸው መስኮች መካከልም የዲፕሎማሲው ዘርፍ ይጠቀሳል፡፡

በ2ዐ16 ዓ.ም አዲስ አበባ ውጤታማ ስራ ከሰራችባቸው ዘርፎች መካከል የዲፕሎማሲው መስክ አንዱ ነው

 ከእህት ከተሞች ጋር የተጠናከረው ግንኙነት

አዲስ አበባ በ2016 ዓ.ም ከነባርና አዳዲስ እህት ከተሞች ጋር ያላትን ግንኙነት የሚያጠናክሩ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ስራዎችን በሰፊው አከናውናለች፡፡ ከእነዚህ መካከልም እህት ከተማ ከሆነችው የደቡብ ኮሪያዋ ቹንቾን ጋር የእህትማማችነት ከተማ ግንኙነት የጀመረበችበት 20ኛ ዓመት በልዩ ሁኔታ ተከብሮ አልፏል፡፡

በኮሪያ ልሳነ ምድር የተነሳውን ጦርነት ለማስቆም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያቀረበውን ጥሪ በመበቀል ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ወደ ደቡብ ኮሪያ በማዝመት ለሀገሪቱ ነፃነት መረጋገጥ መስዋዕትነት ከፍላለች፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ በ1996 ዓ.ም በአዲስ አበባ እና ቹንቾን ከተሞች መካከል የእህትማማችነት ከተማ ስምምነት ተፈርሟል፡፡

የግንኙነቱን 20ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባለፈው ጥቅምት ወር የቹንቾን ከተማ ከንቲባ ዮክ ቶንግ ሃን ከወጣቶች የዲፕሎማሲ ልዑካን ቡድን ጋር ወደ አዲስ አበባ መጥተው በዓሉን በጋራ አክብረዋል፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ ኢትዮጵያ ለደቡብ ኮሪያ ሰላም መጠበቅ ከጎኗ የቆመች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ናት፡፡ ከ6 ሺህ በላይ ወታደሮቿን በማሰለፍ ለሰላም መስፈን ያበረከተችው ጉልህ ሚና፣ ሁለቱ ሀገራት ዛሬ ለደረሱበት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ትልቅ መሰረት የጣለ ነው፡፡

  የደቡብ ኮሪያ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር የተመሰረተውን ዘላቂና ታሪካዊ ወዳጅነት ማሳያ ጀግኖች አርበኞችን የሚዘክሩ መታሰቢያ ሀውልቶችን፣ የባህል ማዕከላትን፣ የባህል ማስተዋወቂያና ማንፀባረቂያ ስፍራዎችን፣ ጎዳናዎች ጭምር በመሰየም ላሳየው አጋር ሊመሰገን ይገባዋል። በሀገር ደረጃና እንደ አዲስ አበባ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የደቡብ ኮሪያ  መንግስት የሚያደርገው ድጋፍ ውጤት እየተገኘበት መጥቷል፡፡ በትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል በመስጠት፣ ለሰራተኞች የስራ ላይ ስልጠናን በማመቻቸት፣ በእሳት አደጋ ስጋት መከላከልና ዝግጁነት ዘርፍ የተለያዩ ድጋፎችን በመስጠት፣ በቴክኖሎጂና በባህል ያለው ግንኙነት እየጎለበተ መጥቷል ብለዋል፡፡

የቹንቾን ከተማ ከንቲባ ዮክ ዶንግ ሃን በበኩላቸው፣ “የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ባትዘምቱልን ኖሮ የአሁኗ ኮሪያ አትኖርም ነበር።— እናንተ ስላላችሁ ነው የኮራነው፡፡ ምናልባት እናንተ የላችሁም ብለን ብናስብ ኮሪያም አትኖርም ነበር፡፡” ሲሉ ኢትዮጵያ ለደቡብ ኮሪያ ነፃነት መረጋገጥ የከፈለችውን ዋጋ አስታውሰዋል፡፡ በቹንቾን ከተማ ከንቲባ ዮክ ዶንግ ሃን የተመራው ልዑክም የለሚ እንጀራ ፋብሪካን ጎብኝቷል፡፡ በደጃዝማች ወንድይራድ ትምህርት ቤት በመገኘት የስፖርት እና የባህል ልውውጥ አካሂዷል፡፡ ከንቲባው በአብርሆት ቤተ መጻህፍት በተዘጋጀው ኮርነር ሁለት ሺህ መጻህፍትንም አበርክተዋል፡፡

ሌላኛው በዓመቱ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሚጠቀሰው የጀርመኗ ላይቭዚግ ከተማ በአዲስ አበባ ስም አደባባይና ትምህርት ቤት ሰይማ መመረቋ ነው፡፡ አደባባዩ በላይቭዚግ እና በአዲስ አበባ መካከል የእህትማማችነት ከተማ አጋርነት 20ኛ ዓመት ሲከበር ሰሞኑን ነው የተመረቀው፡፡ በምርቃት ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የላይቭዚግ ከተማ ከንቲባ ብሩክሀርድ ዩንግ፣ አደባባዩና ትምህርት ቤቱ የሁለቱን ከተሞች የቆየ ትብብር እየተጠናከረ መሄዱን የሚያሳይ መሆኑንና ወደፊት በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ትብብሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባን ወክለው የተገኙት የከተማው አስተዳደር ካቢኔ ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አሻግሬ ገብረወልድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ታሪካዊ በሆነችው በላይፕዚግ ከተማ ላይ አዲስ አበባ የአደባባይና የትምህርት ቤት ስያሜ መሰጠቱ የሁለቱን ከተሞች ትብብር ያለበትን ደረጃ ያሳየ ነው፡፡፡ አዲስ አበባም የአፍሪካ መዲና፣ የተለያዩ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦች መቀመጫ እንደመሆኗ ከላይፕዚግ ከተማ ጋር በተለያዩ መስኮች እያደረገች ያለውን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው የጠቆሙት፡፡

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው፣ “በአዲስ አበባ እና በጀርመኗ ላይፕዚግ የ20ኛ ዓመት የእህትማማችነት፣ የአጋርነት ግንኙነትን በማስመልከት በላይፕዚግ ለከተማችን በስሟ አደባባይ በመሰየሙ የላይፕዚግ ከንቲባ ዩንግን እና አስተዳደራቸውን ላመሰግን እወድዳለሁ። የአደባባዩ መሰየም በቀጣይ በሁለቱ እህት ከተሞች መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚረዳን ነው” ሲሉ አስፍረዋል::

አዲስ አበባ ከጀርመኗ ላይፕዚግ ከተማ ጋር እ.ኤ.አ ከ2004 ጀምሮ የእህትማማችነት ግንኙነት አላት፡፡ ባለፉት ዓመታት፣ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ባለሙያዎች ወደ ላይፕዚግ ከተማ በመሄድ በቅድመ አደጋ መከላከልና በአደጋ መቆጣጠር ዙሪያ ስልጠናዎችን አግኝተዋል፡፡ የላይፕዚግ ከተማ ባለሙያዎች ወደ አዲስ አበባ መጥተው ስልጠናዎችን ሰጥተዋል፡፡ ከስልጠና ባሻገርም የአደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችንና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርገዋል፡፡

2016 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ጋር የእህትማማችነት ግንኙነት ያላት የቻይናዋ ዋና ከተማ ቤጂንግ ከፍተኛ ኃላፊ አዲስ አበባን የጎበኙበት ነበር፡፡ የቤጂንግ ከተማ ኮሚኒስት ፓርቲ ምክትል ዋና ጸሃፊ እና የቤጂንግ የአመራር ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት ሚስተር ሊ ዌይ እና የልዑካን ቡድናቸው ከከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር ተወያይተዋል፡፡ ሁለቱ እህትማማች ከተሞች በትራንስፖርት፣ በቤቶች ግንባታ፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ያለውን ትብብር እንዲሁም የባህልና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይም መክረዋል፡፡

አዲስ አበባ እና ኪጋሊ

ሌላኛው አዲስ አበባ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያደረገችው ውጤታማ እንቅስቃሴ ማሳያ ከኪጋሊ ጋር የተፈረመው የእህትማማችነት ከተማ ስምምነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ ረጅም ጊዜ የቆየ ወዳጅነት እና ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ እና የሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ እንዲሁ በከተማ ፕላን፣ አረንጓዴ ልማት ዙሪያ ልምድና ተሞክሮ የመለዋወጥ የቆየ ግንኙነት አላቸው፡፡ ከአምስት ወራት በፊትም አዲስ አበባ እና ኪጋሊ የእህትማማችነት ስምምነት በመፈረም ግንኙነታቸውን አጠናክረዋል። በዋናነትም ሁለቱ ከተሞች በከተማ ፕላን፣ በቆሻሻ አወጋገድ፣ በአረንጓዴ ከተማ ግንባታ፣ በኢኮ ቱሪዝም፣ በደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ፣ በትራፊክ ማኔጅመንት እና በሌሎች የትብብር መስኮች በጋራ  ለመስራት ነው የተስማሙት፡፡ ይህንን ታሪካዊ ስምምነት በሩዋንዳ ኪጋሊ የተፈራረሙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና የኪጋሊ ከንቲባ ዱሴምግዩንቫ ሳሙኤል ናቸው፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት መገኛና የአፍሪካውያን መሰባሰቢያ መሆኗንና በሁለቱ የአፍሪካ ከተሞች መካከል የተደረገው ስምምነት ትልቅ ትርጉም ያለው እንደሆነ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በወቅቱ ተናግረዋል፡፡ “አፍሪካውያን ኢትዮጵያ ወይም አዲስ አበባን ዋና ከተማቸው አድርገው ነው የሚያዩት፤ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከመሆኗም በላይ የአፍሪካዊነት መንፈስ ለማሳደግ ከበርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ጋር እየሰራች ነው፡፡ በአውሮፓ፣ አሜሪካና ሌሎች አህጉራት የሚገኙ ከተሞች ጋር አብረን እንሰራለን፤ የአፍሪካ ከተሞች አብረው ቢሰሩ የበለጠ ሊማማሩ የሚችሉባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ችግራችን ተመሳሳይ ነው፤ በስነ- ልቦናም ተቀራራቢ ነን፤ በጋራ ብንሰራ የወደፊት ዕድላችን ብሩህ ተስፋ ይሆናል” ነበር ያሉት፡፡

አዲስ አበባ ከኪጋሊ ፅዳት፣ አካባቢን መንከባከብና መጠበቅን በማህበረሰቡ ዘንድ ምን ያህል ባህል እንደሆነ ትማራለች። ኪጋሊም ከአዲስ አበባ ፈጣን እድገት ብዙ መማር እንደምትችል ነው የተገለፀው፡፡

መዲናዋ ልምዷን ያጋራችባቸው መድረኮች

ሊገባደድ ጥቂት ቀናት በቀሩት 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ውጤታማ የሆነችባቸው፣ የሰውን ህይወት የቀየሩ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ዙሪያ ያላትን ልምድ ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከተሞች አካፍላለች፡፡ የአፍሪካ ከንቲባዎች የሊደርሺፕ ኢኒሼቲቭ (AMALI) ከተመሰረተ በኋላ የመጀመሪያ ስብሰባና የልምድ ልውውጥ መድረኩን በአዲስ አበባ ያደረገ ሲሆን የተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎችና የአለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች በመዲናዋ የሚገኙ የቀዳማይ ልጅነት ፕሮጀክቶችን፣ የህፃናት መጫወቻዎችን፣ ትምህርት ቤቶችን እንዲሁም የጤና ተቋሞችን ጎብኝተዋል፡፡ በዚህም የቀዳማይ ልጅነት ፕሮጀክቶች ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች በሞዴልነት የሚወሰድ እና በአፍሪካ ከተሞች ውስጥም መስፋፋት ያለበት እንደሆነ ተመስክሮለታል፡፡

ሌላኛው አዲስ አበባ ተሞክሯዋን ያጋራችበት መድረክ በሞሮኮ ማራካሽ ከተማ የተካሄደው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች መድረክ ነበር። በመድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የተሳተፉ ሲሆን፣ በመድረኩ የአፍሪካ ልማት ባንክ ለከተሞች ልማት የሚውል የ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የድጋፍ እና ብድር አቅርቦት ማፅደቁን ይፋ አድርጓል። የአፍሪካ ልማት ባንክ እና አጋር ድርጅቶች ከሚያቀርቡት የገንዘብ ድጋፍና ብድር ተጠቃሚ ለመሆን አዲስ አበባ መሰረታዊ የልማት ፕሮጀክቶቻችን በማቅረብ አዎንታዊ ምላሽ ያገኘችበት ነበር፡፡

በመርሐ-ግብሩ የተሳተፉ አለም አቀፍ እና አህጉራዊ ተቋማት አዲስ አበባ በፈጣን ለውጥ ውስጥ የምትገኝ፣ የተረጋጋችና ሰላማዊ መሆኗን ጠቅሰው በአዲስ አበባ ከተማ ኢንቨስት ማድረግ አዋጭ እንደሆነ ገልጸዋል።

በትምህርት ቤት ምገባ የተገኘው ዕውቅና

በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ የተከናወነውና በርካታ ሃገራት አባል በሆኑበት የዓለም የትምህርት ቤት ምገባ ጥምረት (School Meal Global Coalition) መድረክ ላይ አዲስ አበባ በሌሎች ሃገራት ልምድ የሚቀሰምባት ከተማ ተብላ የተመረጠችበትም ዓመት ነበር፡፡ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆኑ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ያሳዩት አበረታች ውጤት፣ በምግብ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታ የሚቀር ተማሪ ቁጥር መቀነስ፣ በምገባ ፕሮግራሙ ለእናቶች የተፈጠረው የስራ እድል፣ ፕሮግራሙ ከከተማ ግብርና ጋር ማጣመር በመቻሉ እና የምገባ ማዕከል አቋቁማ በዘላቂነት ፕሮግራሙን በመምራት ያሳየችው አርአያ የሚሆን ስራ በሌሎች ሃገራት ልምድ የሚወሰድበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ እውቅናውን “ትልቅና የሚያኮራ ነው” ሲሉ ነበር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የገለፁት፡፡ 

ሌላው አዲስ አበባ ልምዷን ያጋራችበት መድረክ በሲንጋፖር በተካሄደው የዓለም ከተሞች ጉባኤ ነበር፡፡ በጉባኤው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተሳተፉ ሲሆን፣ በC 40 ከተሞች አባል ከተሞች አማካይነት በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ቀጣይነት ያለው እድገት በማረጋገጥ ለኑሮ ምቹነት እየተሰሩ ስላሉ ስራዎች፣ እድሎች እና ተግዳሮቶች ዙሪያ ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ የወንዝ ዳርቻ ስራዎች፣ የህዝብ መዝናኛ ፓርክ ግንባታ፣ የአረንጓዴ ልማት ንቅናቄ፣ የኮሪደር ልማት ስራዎች ላይ ማብራሪያ የሰጡበት ሁኔታ ነበር።

ከንቲባ አዳነች ከፎረሙ ጎን ለጎን ከC-40 ከተሞች ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ማርክ ዋትስ ጋር በአዲስ አበባ እና በC-40 መካከል ያለውን ትብብር ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ መክረዋል፡፡

በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድና ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም፣ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በማስፋፋት እንዲሁም የህዝብ የጋራ መጠቀሚያ ስፍራዎችን በመገንባት ላይ የተጀመረውን ትብብር ማሳደግን ጨምሮ በሌሎች አብሮ መስራት በሚቻልባቸው አጀንዳዎች ላይ ነው የመከሩት፡፡ አዲስ አበባ እ.ኤ.አ ከ2007 ጀምሮ የC40 ከተሞች ድርጅት አባል በመሆን ባለፉት ጊዜያት የተለያዩ የፋይናንስ፣ የቴክኒካልና የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ስታገኝ ቆይታለች፡፡

ተቀማጭነታቸውን በኢትዮጵያ ካደረጉ የፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ አምባሳደሮች ጋርም የሀገራቱ ከተሞች ከአዲስ አበባ ጋር አብረው ለመስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት የተደረገበት ዓመትም ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ከነበሩት ተሰናባቹ ሬሚ ማርሼ ጋር የደጎል አደባባይን መልሶ ማልማት እንዲሁም ፈጣን የትራንስፖርት አገልግሎትን በጋራ መስራት በሚያስችል ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ከሆኑት ዳረን ዊልች ጋር በኢትዮጵያና እንግሊዝ ከተሞች መካከል የሁለትዮሽ ግንኙነትን በማጠናከር አብሮ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የመከሩበት፣ በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ከሆኑት ኤርቪን ጆዜ ማሲንጋ ጋር በመዲናዋ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ስራዎች እና አዲስ አበባ ከአሜሪካ ከተሞች ጋር ያላትን የእህትማማችነት ግንኙነት ማሳደግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ያደረጋቸው ውይይቶች ከዓመቱ የዲፕሎማሲ ስራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ጉልህ ትርጉም ያላቸው ኹነቶች መስተንግዶ

አዲስ አበባ በዓመቱ ጉልህ ፋይዳ ያላቸው ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና አለም አቀፍ ኹነቶችን፣ ስብሰባዎችንና ጉባኤዎችን በብቃት አስተናግዳለች፡፡ ከእነዚህ መካከልም በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄደውና አንደኛው ጉባኤ በአዲስ አበባ የሚደረገው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ተጠቃሽ ነው፡፡

በዘንድሮ ዓመትም 37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን በርካታ የአፍሪካ ሀገራት እና የተለያዩ ዓለም መሪዎች፣ የአህጉራዊና አለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች በተሳተፉበት በተለመደው መልኩ ፍፁም ሰላማዊና ስኬታማ በሆነ መንገድ አዘጋጅታለች። የፊታችን ከነሀሴ 29 ቀን እስከ ጷጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ታስተናግዳለች፡፡

በጥቅሉ የ2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ከነባርና አዳዲስ እህት ከተሞች ጋር ያላትን ወዳጅነት ለማጠናከር የሰራችበት፣ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶቿ አለም አቀፍ እውቅናን ያገኘችበትና ልምዶቿን ለሌሎች ያካፈለችበት በብዙ መልኩ ስኬታማ የሆነ ዓመት ነበር፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review