የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በመዲናዋ የተሰሩ የልማት ሥራዎችን ለህዝቡ የማሳወቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ እናትዓለም መለሰ ተናግረዋል፡፡
ኃላፊዋ በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች እንዲሁም የማኀበረሰብ አንቂዎች እያደረጉት ባለው ውይይት ላይ በቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የከተማዋ ነዋሪዎችን ሁለተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች መከናውናቸውን አንስተዋል፡፡
በአጭር ጊዜ ተሰርተው የተጠናቀቁ የልማት ሥራዎችም መዲናዋን ከትልልቅ የዓለም ከተሞች ጋር መወዳደር የምትችል ውብ እና ለኑሮ ተስማሚ እንዳደረጓት ጠቁመዋል፡፡

እነዚህን የልማት ሥራዎች ዜጎች በአግባቡ እንዲያውቋቸው በማድረግ ረገድ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ዓለምጸሐይ ሺፈራው በበኩላቸው፣ ከባለሙያዎቹ ጋር እየተደረገ ያለው ውይይት የተሰሩ የልማት ሥራዎች እንዲጎለብቱ እና ክፍተቶች እንዲታረሙ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አመላክተዋል፡፡
“የተደራጀ ኮሙኒኬሽን እና ሚዲያ የሀገራዊ መግባባት ካስማ፤ የትውልድ ግንባታ መሰረት ነው” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የሚዲያ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በሄለን ጀምበሬ