AMN – ሐምሌ 26/2016 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ታሳቢ በማድረግ ሀገራዊ ዕድገትን በሚያስቀጥል አግባብ በጥብቅ ቁጥጥር የሚተገበር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሺዴ ገለጹ
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ፤ በመጀመሪያ እና በ2ኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደት ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ ለመፍባት ግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ ተመን፣ የገንዘብና ፋይናንስ ፖሊሲ፣ የመንግስት ገቢና ወጪ ፊስካል ፖሊሲን በማሻሻልና ዕዳን በማቃለል የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉ በገበያው እንዲመራ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የባንክ፣ ጅምላና ችርቻሮ የንግድ ሰንሰለቶችን ለውጭ ተወዳዳሪ በመክፈት በተቀናጀና በተናበበ ማዕቀፍ ዕድገትን የሚያስቀጠል የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራዊ ባለሃብቱን በመደገፍ የመንግስትን ገቢ በማሳደግና የልማት ድርጅቶችን ውጤታማነት በማሻሻል ጤናማ የንግድ ባንክ ተወዳዳሪነትና የፋይናንስ ሥርዓት መፍጠር በትኩረት እንደሚሰራባቸው አንስተዋል።
የተቀናጀ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተናበበና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክን ጨምሮ በዓለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ የሚተገበር መሆኑን አብራርተዋል።
የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያው እንዲመራ ለማስቻልም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያና በብሔራዊ ባንክ ፍኖተ ካርታ ባለፉት ሶስት ዓመታት ዕቅድ ተይዞ ሲሰራበት እንደነበር አስረድተዋል።
የንግድ ባንክን ከ850 እስከ 900 ቢሊየን ብር ዕዳ ገንዘብ ሚኒስቴር በመውሰድ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ከዕዳ ነፃ እንዲሆኑ በማድረግ ጤናማ የፋይናንስ ሥረዓት ለመፍጠር ወሳኝነት እንዳለው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስቀጠል በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና አበዳሪ ሀገራት ድጋፍ ተግባራዊ መደረጉ ዕዳን በመቀስ የውጭ ምንዛሬ ክምችትን ለማሳደግ አመች መሆኑን ተናግረዋል።
የፖሊሲ ትግበራውን በከፍተኛ ቅድመ ዝግጅትና ጥንቃቄ በመምራት የዋጋ ንረትና የምንዛሬ ገበያ መዋዠቅን እንዲሁም የአጭር ጊዜ ጫናን በመቋቋም የተረጋጋ ኢኮኖሚ መፍጠር ዋነኛ ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የፖሊሲ ትግበራና ድርድሩም የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት በማስቀደም የተፈጸመ እና የተገኘው የ4 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ ቁጠባ ድጋፍ የዕዳ ጫናን ለማቃለል ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የገንዘብ ድጋፉ የሀገርን የዕዳ ጫና በማቃለል ለዝቅተኛ ተከፋይ ሠራተኞች፣ ለከተማና ገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች፣ ለማዳበሪያ፣ ለነዳጅ፣ ለዘይት ድጎማ እና ለመደበኛ የልማት ሥራ የሚውል መሆኑን አንስተዋል።
የገንዘብ ድጋፉም በጥብቅ የቁጥጥር ማዕቀፍ በቂ ዝግጅት ተደርጎበት በግልጸኝነት ለልማት ስራና በሪፎርሙ ምክንያት ጫና ሊደርስባቸው የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጎማ የሚውል መሆኑን ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚመራው የማክሮ ኢኮኖሚክ ቡድን ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ዜጎች ድጎማ የሚሆን የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን አስረድተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና በገንዘብ ሚኒስቴር ትብብር ለደመወዝ ድጎማ የሚውል የፋይናንስ ቅድመ ዝግጅት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በዚህም የፌደራልና የክልል ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ድጎማ ከ90 እስከ 95 ቢሊየን ብር የሚደርስ ገንዘብ በፌደራል መንግስት ወጪ ተሸፍኖ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በነዳጅ ድጎማ እስከ 100 ቢሊየን ብር የሚደርስ ድጎማ ማድረግ የሚያስችል በጀት መያዙን ገልጸዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ፣ አርሶና አርብቶ አደሩ፣ ህግ አስከባሪዎች እንዲሁም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን በመወጣት ለፖሊሲ ትግበራ ውጤታማነት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።