AMN-ኅዳር 16/2017 ዓ.ም
የማዕድን ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖን ጎብኝተዋል።
የማዕድን ዘርፉ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የማዕድን ሀብት እንዳላት የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ዓመት የወርቅ እና ሌሎች ማዕድናት የወጪ ንግድ መጠን መጨመሩን ተናግረዋል።
ኤክስፖው በማዕድን ዘርፍ ያሉ እምቅ ሀብቶችን ያስተዋወቅንበት፣ ኢንቨስተሮች ማዕድንን እሴት ጨምረው ወደ ውጭ የገበያ ትስስር የፈጠሩበት መሆኑን ገልጸዋል።
መንግሥት ህገ ወጥ የማዕድን ግብይት ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑ እና ፋብሪካዎች ወደ ስራ በመግባታቸው ጭምር በዘርፉ ከፍተኛ ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል።
በቀጣይም የባህላዊ የማዕድን ማውጣት ሂደትን በማስቀረት ግዙፍ ፋብሪካዎችን ማስፋፋት ላይ ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህም ቴክኖሎጂ መር ምርት እና እሴት መጨመር ላይ ትኩረት በመስጠት ለምርት ጥራት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ዘርፉ እያስገኘው ያለው ውጤት የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን በጎ ጅማሮ አመላካች እንደሆነ ተናግረዋል።
በመሆኑም እምቅ የማዕድን ሀብታችንን በመጠቀም የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በማዕድን ፍለጋና ምርት መሠማራት የሚፈልጉ ኩባንያዎች እንዲሰማሩም መንግስት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
በኤክስፖው የማዕድን አምራቾችና ላኪዎች፣ የማዕድን ተጠቃሚዎች፣ የቴክኖሎጂ አምራቾችና አቅራቢዎች ምርትና አገልግሎታቸውን እያስተዋወቁ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!