የማይተኙ ከተሞች

ከተሞች የሀገራት የልብ ምት፣ የስልጣኔ መግቢያ በር፣ የምጣኔ ሀብት ርካብ፣ ቀን ነፍስና ስጋን ማስደሰቻ፤ ማታ ደግሞ ጨለማውን መርቻ የድል መቅረዝ ናቸው፡፡ የከተማ ኑሮ መሻሻል ምርታማነትን፣ ባህልን እና የሰው ልጆችን ደስታ ከፍ በማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት የከተማ ልማት ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ግሌዘር ይናገራሉ፡፡

በተለይም ቀን እንደ ፀሐይ ደምቀው፣ ማታ እንደ ክዋክብት ፈክተው የሚታዩ ከተሞች የዓለማችን ሕይወት መቀጠል ምልክት፣ የልብ ትርታችን ምት ናቸው ሲሉም እንደ ላስቬጋስ፣ ሎሳንጀለስ፣ ቶኪዮና ሎንደንን የመሳሰሉ ከተሞችን በዋቢነት እየጠቃቀሱ የማይተኙ ከተሞችን ባማሩ ቃላት ያሞካሿቸዋል፡፡

በከተሞች ኢኮኖሚና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥናታዊ ጽሑፎችን እና መፅሐፍትን ያሳተሙት ፕሮፌሰር ኤድዋርድ እ.ኤ.አ በጥር 31 ቀን 2012 “የከተሞች እውነት ወይም ድል” (Triumph of the City) የተሰኘ ግሩም ጥናታዊ መፅሐፍ አሳትመዋል፡፡

በርካታ የዓለማችን ክፍል ቀን እንደነገሩ ውሎ አመሻሹን ሲያሸልብ ከተሞች ግን በተራራ ላይ እንደተለኮሰ ችቦ ብርሃንን እየፈነጠቁ በምድሪቱ ላይ ያረበበውን ጨለማ እንደ አደይ አበባ በፈካ ውበታቸው እንዴት እንደሚገፍፉት ፕሮፌሰር ኤድዋርድ በአማረ አገላለፅ በመፅሐፋቸው ከሽነውታል፡፡

ኒውዮርክ ብዙ ጊዜ “የማትተኛዋ ከተማ” እየተባለች ትጠራለች፡፡ ከተማዋ ቀን በተፈጥሮ ብርሃን ከፀሐይ ጋር ደምቃ ትውልና መሸት ሲል ደግሞ ከላይ በጨረቃና ክዋክብት፣ ከታች በዘመናዊ መብራቶች ትዋባለች፤ ትደምቃለች፡፡

ይህንን ተከትሎም እንደ ወፈ ሰማይ ከበዛው ነዋሪዋ ባሻገር በርካቶችን ስለምትስብ በቱሪዝም ዘርፍ ብቻ በአሜሪካ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላት ድርሻ ከፍ ያለ ነው፡፡ ለአብነትም እ.ኤ.አ በ2023 ከቱሪዝም ብቻ 74 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አመንጭታለች ይላል የዓለም የጉዞ እና ቱሪዝም ምክር ቤት (WTTC) እ.ኤ.አ በሚያዚያ 4 ቀን 2024 ይፋ ባደረገው መረጃ፡፡

እንደ መረጃው ከሆነ በከተማዋ ያሉ በዓለም ታዋቂ የሆኑ ሙዚየሞች፣ ቴአትር ቤቶች እና ፌስቲቫሎች እንዲሁም የከተማዋ የባህል ስጦታዎች እና የቀኑን ድካም ማስረሻ የምሽት ቤቶች ጎብኚዎችን በመሳብ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።

የቱሪዝም ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ ከመዝናኛ ባሻገር ነው፡፡ ለአብነትም እንደ መስተንግዶ፣ ችርቻሮ እና ትራንስፖርት ያሉ ዘርፎችን ያጠቃልላል። ይህንንም ተከትሎ ቀን ሳይዝሉ ማታ ሳያንቀላፉ 24 ሰዓታት ንቁ የሆኑ ከተሞች ለሀገራት ብልፅግና ድርሻቸው እንዲህ በቀላሉ እንደማይታይም የከተማ ኢኮኖሚ ምሁሩ ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ግሌዘር በመፅሐፋቸው ያብራራሉ፡፡

የዓለም የጉዞ እና ቱሪዝም ምክር ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ ከተሞች ልክ እንደ ኒዮርክ የባህል አብዮትን ከኢኮኖሚያዊ ከፍታ፣ ፅናት እና ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ማዋሃድ ከቻሉ እና እንደቀኑ ሁሉ ሌትም ንቁ ከሆኑ ለሀገራቸው ከፍታን፣ ለዜጎቻቸው ሁለንተናዊ ብልፅግናን የማጎናፀፍ ኃይላቸው ብርቱ ነው፡፡

የማያንቀላፉ የዓለማችን ከተሞች ፀሐይ ወደማደሪያዋ ስታዘቀዝቅ በውበታቸው ብርሃን፣ ጨለማውን እየሰነጠቁ ወደ ደማቅ የሌሊት ማዕከልነት ይለወጣሉ፡፡ እነዚህ ከተሞች የመዝናኛ ስፍራዎቻቸው እንደቀኑ እንዲፈኩ ይበልጥም ሳቢነታቸው እንዲጨምር ከከዋክብትና ከጨረቃ ብርሃን ጋር የሚወዳጁ ሰው ሰራሽ መብራቶችን ይጠቀማሉ፡፡

ባህልና ወጋቸውን፣ አረፍ ማለት ያሻውን የህብረተሰብ ክፍል በማይረብሽ መልኩ ለስለስ፣ አንዳንዴም ሞቅ ያሉ ሙዚቃዎችን ከፍተው ሌቱን ቀን ያስመስሉታል፡፡ በዚህም እንኳን የውጭውን ይቅርና የሀገሬው ሰው መንጋቱን ብቻ ሳይሆን መምሸቱን እንዲናፍቅ ያደርጉታል ይላል የዓለም የጉዞ እና ቱሪዝም ምክር ቤት መረጃ፡፡

ዋና መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ዓለም አቀፉ አስጎብኝ ድርጅት ኤግዞቲካ ‘Exoticca’ በማህበራዊ ትስስር ገፁ (Exoticca Blog) ላይ ከሰሞኑ “በምሽት የሚደምቁ ከተሞች” (Best cities for nightlife around the world) ሲል ይፋ ባደረገው መረጃ ላይ እንደገለፀው ከአሜሪካ ከተሞች ኒዮርክን እንደጠቀስነው ሁሉ የጀርመኗ መናገሻ በርሊን በአውሮፓ ምድር የቀን ፀሐይ የሌትም ጨረቃ ናት፡፡

በአውሮፓ ውስጥ ለምሽት ንግድ እጅግ ተመራጭ ከሆኑ ከተሞች በርሊንን በዋቢነት ያነሳው መረጃው፣ ከተማዋ የትናንት ወዝና ደርዝ ያለውን ታሪኳን ከዛሬ ማንነቷ እና ከዓለም ተጨባጭ እውነታ ጋር አስማምታ ነገዋንም ቀድማ እየሰራች በመቀጠሏ እንኳን ቀኗ ምሽቷም ብርሃናማ፣ ብራማም ነው ይላል መረጃው፡፡ በዚያው ልክ ከተማዋ በጀርመን ኢኮኖሚ ያላትን ቦታ ሲጠቁም፡፡

በርሊን ከገዘፈ ታሪኳ ባሻገር፣ በምሽት የንግድ እንቅስቃሴዋ፣ በታዋቂ የዳንስ ቤቶቿ እና በሙዚቃ ባህሏ ትታወቃለች። ከጨለማ በኋላ ያለው የበርሊን ገጽታ ታሪካዊ አመጣጥ እንዳለው የጠቀሰው መረጃው፣ ይሄውም እ.ኤ.አ ህዳር 9 ቀን 1989 የበርሊን ግንብ መፍረስን ተከትሎ በከተማዋ ያሉ በርካታ ሕንፃዎች እና መሰል ታሪካዊ ስፍራዎች የደራረቀና አስፈሪ ገፅታቸውን በሰላም እና በነፃነት ወዝ አለስልሰው የጀርመናውያን የነፃነት አደባባይ ሆነዋል፡፡ እናም ከተማዋ የስጋም፣ የመንፈስም ግንብ ሳይከልላት

ዳር እስከ ዳር ቀን ብቻ ሳይሆን ምሽትም ትደምቃለች፡፡

የእንጊሊዟ ለንደን ደግሞ ሌላኛዋ የምድራችን የማታንቀላፋ ከተማ ናት። በደማቁ የምሽት ንግድ አብዝታ ትታወቃለች፤ በከተማዋ ያለው የምሽት ሕይወት ለሁሉም የሚስማማ ነው፡፡ አቅምን ያገናዘቡ እና ጨለማን የሚያስረሱ ልዩ ልዩ የመዝናኛ ስፍራዎችም ያሏት ከተማ እንደሆነች በመረጃው ተመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያዊው የሙዚቃ ንጉስ የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ

እሩቅ ምስራቅ ሳለሁ፡ ጃፓኗን ወድጄ፣

ትዝ ትለኛለች በፍቅሯ ነድጄ፡፡

በመርከብ ሽር ሽር ለሷ የሚስማማ፣

እራቷ ቶክዮ  ምሳ ዮከሀማ…፡፡  ሲል እንዳደነቃት ጃፓናዊቷ ቶክዮ ሌላኛዋ የማትተኛ የምድራችን ከተማ ናት ይላል ኤግዞቲክ የተሰኘው ዓለም አቀፉ አስጎብኝ ድርጅት በሰሞነኛ መረጃው። በውበታቸው፣ በጠንካራ ሰራተኝነታቸው በስነ ምግባራቸውና በጨዋታ አዋቂነታቸው የሚታወቁት ጃፓናውያን በቶኪዮ ከተማ ቀን ብቻ ሳይሆን ሌትም  ከእንግዶቻቸው ጋር ፈክተው ይታያሉ፡፡

በከተማዋ ያሉ የተለያዩ ንግድ ቤቶች፣ በተለይም ምግብ ቤቶች፣ ክለቦች፣ ሱፐር ማርኬቶችና መሰል ልዩ ልዩ ተቋማት እንደ ቀኑ ሁሉ በቶክዮ ክፍት ናቸው። ክፍት ብቻ ሳይሆኑ ተጨማሪ ውበትን የሚያጎናፅፉ ልዩ ልዩ መብራቶችንና ጌጣጌጦችንም በመጠቀም የውበትን ሸማ ተጎናፅፈው የምድር ክዋክብት ሆነው ይታያሉ፡፡ በዚህም ከተማዋ ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኝዎች ምቹ ከመሆን ባሻገር በስራም ቢሆን 24/7 ንቁ ናትና የጃፓን ኢኮኖሚ ከፍታ ምንጭ ሆናም ታገለግላለች ይላል መረጃው፡፡

እነዚህ የማያንቀላፉ የዓለማችን ከተሞች እንደ ቀኑ ሁሉ በምሽት እይታዎቻቸው ዓይንን ከመማረክ ባለፈ ጉልህ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አላቸው ይላሉ ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ግሌዘር፡፡

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለፃ የማያንቀላፉ ከተሞች ጎብኝዎችን ከተለያዩ የዓለማችን ክፍል ከመሳብ ባሻገር ነዋሪዎቻቸው በስራ ብርቱ እንዲሆኑ፣ ፈጠራዎች ላይ እንዲጠነክሩና በአካልም በአዕምሮም የነቁ እንዲሆኑ እገዛ ስለሚያደርጉ ሀገራት ከተሞቻቸው፡- ትናንትን የሚያስታውሱ፣ ዛሬን በልኩ ሆነው የሚገኙ፣ መጭውንም በውል የተረዱ የበቁና የተዘጋጁ ሆነው እንዲገኙ መስራት አለባቸው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ከፍታቸው ይጨምራል ይላሉ ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ግሌዘር፡፡

የማይተኙ የከተሞች ውበት በህንፃ ግንባታቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በሚፈጥሩት አውድ ላይ የተመሰረተ ነው። ለአብነትም ከሕንፃዎቻቸው እና መሰል ውበቶቻቸው ባሻገር በቀንም ሆነ በሌሊት የማያቋርጥ እንቅስቃሴዎች ከተሞችን ወደ ንቁ እና ሕያው አካላት እንደሚለውጧቸውም ፕሮፌሰሩ ጠቅሰዋል፡፡

አብዛኛዎቹ የማይተኙ ከተሞች ዘመናዊና ሰማይ ጠቀስ ፎቆቻቸውም ቢሆኑ ከታሪካዊ ምልክቶችና ህብራዊነታቸው ጋር ተጣጥመው ያለፈውን፣ የአሁኑን እና የወደፊቱን አሳማኝ ምስላዊ ትረካ የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ይህም ድባባቸው ቀልብን ይማርካል፡፡ ነፍስያን ያረካል፡፡ ከተሞቹ ከዘመኑ የታረቁ ብቻ ሳይሆኑ ትናንትን የሚያስታውሱ በመሆናቸው የባህል ሀብታም ያደርጋቸዋል፤ ይህም ሌላ ገቢ፤ ሌላ አቅም ነው፡፡

የስነ ልቦና ምሁራን የማይተኙ ከተሞችን “የዓለም የልብ ምት ናቸው። ምክንያቱም ሃያ አራት ሰዓት ስለማያንቀላፉ፣ ዓለማችን ሕይወት ዘርታ እንድትኖር ያደርጋሉና” ሲሉ ይገልጿቸዋል። ዋና መቀመጫውን ቶኪዮ ያደረገው “ዘ ጃፓን ታይምስ” የተሰኘው የሚዲያ ተቋም በ2023 “የማያንቀላፉ ከተሞች” ሲል በሰራው ጥናታዊ ዘገባም ይህ እውነት ሰፍሮ ይገኛል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review