ተጫዋቹ ከጉልበቱ በታች ያለው የግራ እግሩ ክፍል ሁለቱም አጥንቶቹ ተሰብረዋል። ይህ አጋጣሚ ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ ስብራቱ በህክምና አጠራሩ (Left Mid shaft Tibial and Fibula Fracture) የገጠመው የወልዋሎ አዲግራት እግር ኳስ ክለብ የተከላካይ መስመር ተጫዋች እያሱ ለገሰ ነበር፡፡ ከሰሞኑ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እያደረጉ በነበሩት ጨዋታ ጅማሮ ነው ይህ አደጋ የተከሰተው፡፡ ተከላካዩ እያሱ ወደሜዳ የሚመለስበት ወቅትም አልታወቀም፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥም በተለያየ ወቅት በተጫዋቾች ላይ እየደረሰ ያለውን የጉዳት ዜናዎችን ስንሰማ ቆይተናል፡፡
የማንችስተር ሲቲው አማካይ ሮድሪ የጉልበት ጅማት መበጠስ ጉዳትም ከሰሞኑ ከወደ አውሮፓ ከተሰሙ የጉዳት ወሬዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ስፔናዊው አማካይ በ5ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ማንችስተር ሲቲ ከአርሰናል በነበረው ጨዋታ ተጎድቶ 21ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ መውጣቱ ይታወቃል። የተጫዋቹ ጉዳት እስከ ውድድር አመቱ መጨረሻ ድረስ ወደሜዳ እንደማይመለስ የክለቡ መረጃ ያሳያል። ሮድሪን መተካት ከባድ መሆኑን ያሳወቀው አሰልጣኙ እሱ በተሰለፈባቸው ያለፉት 48 የሊግ ጨዋታዎች ክለቡ ውጤታማ መሆኑን እና ተጫዋቹን ለመተካት መፍትሄ እንደሚፈልጉም አሳውቀዋል።

የባርሴሎናው ግብ ጠባቂ ማርክ አንድሬ ቴርስቴገንም እንደዚሁ የጉልበት ቀዶ ጥገና እንደሚያደርግ ስካይ ስፖርት የዘገበው ከቀናት በፊት ነበር፡፡ በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ቪያሪያልን 5 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ ጉዳት ያጋጠመው አምበሉ ቴርስቴገን ከባድ ጉዳት ያስተናገደ ሲሆን፣ የ32 አመቱ ግብ ጠባቂ በ2014 ከጀርመኑ ክለብ ቦርሲያ ዶርትመንድ ባርሴሎናን ከተቀላቀለ በኋላ 400 ጨዋታዎችን ማድረግም ችሏል፡፡ ተጫዋቹ ለ8 ወራት ከሜዳ እንደሚርቅ እየተዘገበ ሲሆን፣ ባርሴሎና በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ተጠባባቂ ግብ ጠባቂዎችን እንዲጠቀም ያስገድደዋልም ተብሏል፡፡
በእርግጥ በጉዳት መጠናቸው ከበድ ያሉትን በአስረጅነት አነሳን እንጂ የያዝነው የውድድር ዘመን በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ብቻ 80 ተጫዋቾች ጉዳት አስተናግደው ከሜዳ ርቀዋል። የተራዘመ የጨዋታ መርሃ ግብር በተጫዋቾቹ አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት በአውሮፓ 5ቱ ታላላቅ ክለቦች ከፍተኛ ብቃት ባላቸው ተጫዋቾች መካከል ተደጋጋሚ ጉዳት ይደርስባቸዋል። የሻምፒየንስ ሊግ እና የኢሮፓ ሊግ መስፋፋት፣ ረጅም ውድድሮች እና የዓለም ክለቦች ዋንጫ ተጫዋቾች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የስራ ጫና የጉዳት መጠንኑ እንዳባባሰው ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
እግር ኳስ ብዙ ንክኪዎች የሚስተናገድበት የስፖርት ዓይነት ነው፡፡ በዚህ ንክኪ መካከል ተጫዋቾች የተለያዩ ጉዳቶችን ያስተናግዳሉ። ከቀላል የጡንቻ መሳሳብ ጀምሮ እስከ ከባድ የቀዶ ጥገና ህክምና እስከሚፈልግ የጉዳት ዓይነት ድረስ። እነዚህ ጉዳቶች አንዳንድ ጊዜ እስከ የአጥንት መሰበርም ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ተጫዋቾች ከጉዳታቸው አገግመው ወደ ሜዳ ለመመለስና በጥሩ ሁኔታ ቀድሞ በነበራቸው አቋም ላይ ዳግመኛ ለመገኘት የሚወስድባቸው ጊዜ በጣም ረጅም ይሆናል፡፡
በኢትዮጵያም በርካታ ተጫዋቾች ለጉዳት ይዳረጋሉ፡፡ በየክለቦቻቸው የህክምና ቡድን እንደጉዳታቸው መጠንም ህክምና ይደረግላቸዋል። ሆኖም ተጫዋቾች ከጉዳት በማገገማቸው ሂደት ውስጥ ያላቸው ውጤታማነት ከስነ ልቦና ጥንካሬያቸው ጋር የተያያዘ በመሆኑ ተመሳሳይ ጉዳት ደርሶባቸው እንኳን ወደ ሜዳ ለመመለስ አንደኛው ሲዘገይ ሌላው ደግሞ ሲፈጥን ይታያል።
በስፖርት ዘርፍ የህክምና ስራ እየሰሩ የሚገኙት የህክምና ባለሙያው አስራት ለገሰ በሰጡት አስተያየት ስለተጫዋቾች ጉዳት ተጠይቀው “ከበድ ያሉ ጉዳቶች በሚያጋጥምበት ወቅት ወደ ሜዳ ለመመለስ የሚደረጉት ሥራዎች ጊዜን የሚወስዱ እና ትዕግስትን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ የህክምና እርዳታ አልያም የቀዶ ህክምና ከተደረገ በኋላ የሚኖረው የማገገሚያ ጊዜ የስነ ልቦና ጥንካሬን እና ተስፋ አለመቁረጥን ይጠይቃል” ሲሉ ተናግረዋል።
የበርካታ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ጠንቅ የሆነው ተደጋጋሚ ጉዳት ይዞት የሚመጣው ፍርሃትና ስጋትም በተጫዋቾች ቀጣይ የእግር ኳስ ጨዋታ ስኬታማነት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በተደጋጋሚ ጉዳት ምክንያት የእግር ኳስ ህይወታቸው የሚበላሽባቸው እንዳሉ ሁሉ ከጉዳታቸው ጋር ታግለውም ለታላላቅ ስኬት መብቃት የቻሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ይህን በተመለከተ የህክምና ባለሙያው አስራት ሲናገሩ “አንዳንድ ተጫዋቾች ዘለግ ላለ ጊዜ ከጨዋታ ቢርቁም በርትተው በመስራት አቋማቸው ሳይወርድ ወደ ሜዳ ሲመለሱ እንመለከታለን። ይህ መሆን የቻለው ከባለሙያው ክትትል ጋር የቤተሰብ ድጋፍና የተጫዋቾቹ ጥንካሬ ሲደመር ነው” ብለዋል፡፡
ተጫዋቾች የስነ ልቦና ጫና ሳይደርስባቸው በቶሎና በቀደመ አቋማቸው ወደ ሜዳ እንዲመለሱ ከተፈለገ ዘመናዊ የሆነ የማገገሚያ መርሃ ግብርና አስፈላጊ መሣሪያዎች ያስፈልጋሉ የሚሉት የህክምና ባለሙያው አስራት የብቁ ባለሙያዎች መኖር ደግሞ የበለጠ ወሳኝ ነው፡፡ ክለቦች ጉዳት ላይ ያሉ ተጫዋቾቻቸውን የሚይዙበትና የሚከታተሉበት መንገድ ክፍተት አለበት፡፡ ክለቦች ጉዳት ላይ ያሉ ተጫዋቾቻቸውን መከታተል፣ መንከባከብና በቂ ትኩረት የሚያገኙበትን አሠራር መዘርጋታቸው ለክለቦቹ መሠረታዊ ጉዳይ መሆን አለበት ሲሉ ሀሳባቸውን ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት በሚፈለግበት ደረጃ ላይ እንዳይገኝ በርካታ ጎታች ምክንያቶች እንዳሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ። ከእነዚህም መካከል ብሄራዊ ቡድኑን ጨምሮ ክለቦች ጠንካራ አደረጃጀት አለመያዛቸው አንዱ ነው፡፡ የህክምና ባለሙያው አስራት ለገሰም በስፖርት ላይ የሚደርስ ጉዳት የተለየ ትኩረት ይፈልጋል ባይ ናቸው፡፡ ክለቦች ጠንካራ የጤና አደረጃጀት እንደዚሁም በባለሙያዎች የሚመራ ዘመናዊ አደረጃጀት ሊኖራቸው እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡
የእግር ኳስ ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው እያደረጉት ያለው የጤና ክትትል ምን ያህል ነው? ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ጅምሮች ያሉ ቢሆንም በበቂ ደረጃ አለ ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡ በተለይም የባለሙያ እጥረት፣ የህክምና መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ ያለመኖር እና ክለቦች ከፍተኛ የሆነ የበጀት ችግሮች ምክንያት ክለቦች ጠንካራ ስራ እየሰሩ ነው ማለት አይቻልም ሲሉም አስረድተዋል፡፡
የተጫዋቾችን ጤና በመከታተሉ ረገድ በሚፈለገው ደረጃ እየተሰራ ነው ብዬ ለመናገር አልደፍርም ያሉት ባለሙያው አስራት ለገሰም፣ ተጫዋቾች የደረሰባቸው የጤና እክል ሳይታወቅ ጭምር ለረዥም ጊዜ በጨዋታ ላይ እንደሚያሳልፉም ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ተጫዋቾች ለከፋ ጉዳት እንደሚጋለጡ እና ጉዳት የደረሰባቸው ተጫዋቾችም በቂ ህክምና ሳያገኙ ትንሽ ሲሻላቸው ተመልሰው ወደሜዳ ሲገቡ እንደሚታዘቡ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ብዙ ጊዜም ተጫዋቾች ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስባቸው ከክለቦቹ አቅም በላይ ስለሚሆን ወደ ሆስፒታል ሄደው እንደሚታከሙ አንስተዋል፡፡
በአጠቃላይ ምንም እንኳን የስፖርት ህክምና ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ ቢሆንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት በሚፈለግበት ደረጃ ላይ እንዲገኝ ከተፈለገ የጤናውን ዘርፍ ማዘመን ግድ ነው፡፡ በቴክኒክ፣ ታክቲክና በስነ ልቦናው ረገድ ጠንካራ ክለቦች ለመፍጠርም ሁነኛው መንገድ ስፖርቱን በባለሙያ መምራት ነው፡፡
የእግር ኳስ ጨዋታ አጭር የስራ ቆይታ የሚደረግበት እየተባለ በእግር ኳስ ባለሙያዎች ይገለፃል። እስካሁን ባለው ልምድ መሰረትም 15 ዓመት በአማካይ ተጫዋቾች በእግር ኳስ የሚቆዩበት ጊዜ ነው። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ታዲያ ምንም እንኳን ህጉ መጥፎ ጨዋታን ቢከለክልም እግር ኳሱ ብዙ ጉዳቶች በስፖርቱ ላይ ብዙ ጊዜ የሚጎዱበት መሆኑ ይታወቃል። የስፖርቱ ባህሪ በራሱ የሚፈጥረው የጤና እክል እንዳለ ሆኖ ለተጫዋቾች በቂ የሆነ የህክምና ክትትል ባለመደረጉ የሚደርስ ጉዳት እንዳለም ከ20 ዓመታት በላይ የስኮትላንድ እግር ኳስ ማህበር ሐኪም ሆነው ያገለገሉት ዶክተር ጆን ማሊን ይገልጻሉ፡፡
ለአንድ የእግር ኳስ ቡድን በጣም አስፈላጊና አስገዳጅ ከሆኑ የዘመናዊ እግር ኳስ መገለጫዎች አንዱ የስፖርት ሕክምና ነው፡፡ ዛሬ ላይ በተለያዩ አገሮች በተራራቀ ቴክኖሎጂ ታግዞ እየተካሄደ ያለውን የሕክምና ዘርፍ ለተመለከተ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ምን ላይ ይገኛል? ብሎ መጠየቅ አይቀርም። በአውሮፓና በሌሎችም አህጉራት የሚገኙ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ለሚገጥማቸው አነስተኛ ጉዳት ሳይቀር በመመርመሪያ መሣሪያ ታግዞ የሚደረግላቸው ሕክምና አንድም የተጫዋቾቹን ደኅንነት ጠብቆ ለረዥም ጊዜ በእግር ኳስ ጨዋታ እንዲዘልቁ ሲረዳ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተጫዋቾቹ የሚጫወቱበት ክለብ ስኬት አስተማማኝ ሲያደረገው ይስተዋላል፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ